በሙሴ ታሪክ ላይ በመመርኮዝ ብዙ የሙስሊም ኡሌማዎች (ምሁራን) ሰው ነቅቶ እያለ በዚህ ዓለም ላይ የአላህን መገለጥ ማየት አይችልም ብለዋል፡፡ “ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ፡- ጌታዬ ሆይ (ነፍስህን) አሳየኝ ወደ አንተ እመለከታለሁና አለ፤ (አላህም) - በፍጹም አታየኝም፣ ግን ወደ ተራራው ተመልከት፤ በስፍራውም ቢረጋ፣ በእርግጥ ታየኛለህ አለው፤ ጌታውም ለተራራው በተገለጸ ጊዜ ንኩትኩት አደረገው፤ ሙሳም ጮሆ ወደቀ፤ በአንሰራራም ጊዜ፣ ጥራት ይገባህ፣ ወዳንተ ተመለስኩ፤ እኔም (በወቅቱ) የምእምናን መጀመሪያ ነኝ አለ” (ሱረቱ አለ-አዕራፍ 7፡143)፡፡
ሃዲዝ የሚያረጋግጠው “እንዲህም አለ፡- ጌታውን አይቶ እንደሆነ ልጠይቀው ፈለግሁ. አቡ ዳሃር እንዲህ አለ፡ እኔ ግን ጠይቄዋለሁ፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፡ ብርሃን ነበር ያየሁት” (ሳሂህ ሙስሊም)፡፡ በሌላ ሃዲዝ እንዲህ ይላል፤ “አቡ ዳሃር እንደተናገሩት፣ የአላህን መልዕክተኛ እንዲህ ብዬ ጠየኳቸው፡- ጌታዎትን አይተዋል? እሳቸውም (እርሱ) ብርሃን ነው፤ እንዴት ላየው እችላለሁ? ሲሉ መለሱ” (ሳሂህ ሙስሊም)፡፡ ሃዲዙ ትርጉሙን እንዲህ ሲል ያብራራል፡- “አላህ አይተኛም፤ መተኛቱም አግባብ አይሆንም፡፡ ሚዛኖቹን ቀና እና ዝቅ ያደርጋል፡፡ ማታ የሚሰራው ሥራ ወደ እርሱ ሳይደርስ ቀን የተሰራው ሥራ ወደ እርሱ መቅረብ አለበት፡፡ እንደዚሁም ቀን የሚሠራው ሥራ ወደ እርሱ ከመቅረቡ በፊት ማታ የተሠራው ሥራ በፊቱ መቅረብ አለበት፡፡ ፊቱ የተሸፈነው በብርሃን ነው፡፡ ሽፋኑን ቢያነሳ እይታው እስከደረሰበት ቦታ ሁሉ የፊቱ ክብር ፍጥረታቱን ሁሉ ያቃጥላል” (ሳሂህ ሙስሊም)፡፡
ሁሉን የሚችለው የአላህ ክብር ቢገለጥና በእርሱና በእኛ መካከል ያለው ብርሃን ቢነሳ ኖሮ ፍጥረት ሁሉ በታላቅ ብርሃኑ ይቃጠል ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ሰው ነቅቶ እያለ አላህን ማየት አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ አላህን በሕልም መገለጥ ማየት ይፈቀዳል፡፡ ይህንንም ኢማም አህመድ አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህ ነው አላህ ፊቱን ከነብዩ ከሙሳና ከእኛም የሰወረው፡፡ አላህ ከመጋረጃ በስተጀርባ ለሰው ልጆች ይገለጣል፡፡ አላህ ብርሃኑን፣ ክብሩንና ታላቅነቱን ቢገልጥ ምድርና ፍጥረቷ በሙሉ ይቃጠላሉ፡፡
አላህ ራሱን ለሰዎች መግለጥ ቢፈልግ እንዴት አድርጎ ነው የሚገልጠው? ብርሃኑ በሌላ ነገር ውስጥ አልፎ መታየቱ ግዴታ ነው፡፡ ቁርዓን እንዲህ ይላል፡- “አላህ የሰማያትና የምድር አብሪ ነው፡፡ የብርሃኑ ምሳሌ በውስጧ መብራት እንዳለባት (ዝግ) መስኮት መብራቱ በብርጭቆ ውስጥ የኾነ ብርጭቆይቱ ፍፁም ሉላዊ ኮከብ የምትመስል፤ ምሥራቃዊው ምዕራባዊም ካልኾነች ከተባረከች የወይራ ዛፍ ዘይቷ እሳት ባይነካውም እንኳ ሊያበራ የሚቀርብ ከኾነች (ዘይት) የሚቃጠል እንደሆነ (መብራት) ነው፡፡ አላህ ወደ ብርሃኑ የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡ አላህም ለሰዎች ምሳሌዎችን ያቀርባል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው” (ሱረቱ አል ኑር 24፡35)፡፡ ይህ አያ (ጥቅስ) ግልጽ እንደሚያደርገው፤ አላህ ብርሃኑን በብርጭቆ ፋኖስ ውስጥ በመሸሸግ ይህን ፍጥረተ-ዓለም በእውቀቱ እንደሚያበራ ነው፡፡ ራሱን ለሰዎች ሁሉ እንዴት እንደሚገልጥ ሊያሳየን አላህ ይህን ምሳሌ አስቀመጠልን፡፡
እንደዚሁም፤ ቁርዓን በዮም አልቅያማ (በትሳኤ ቀን) ሰዎች አላህን እንደሚያዩ ይናገራል፡፡ “መጨረሻይቱንም (ዓለም) ትተዋላችሁ (አትዘጋጁላትም)፡፡ ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው፡፡ ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው” (ሱረቱ አል-ቅያማ 75፡21-23)፡፡ በገዛ አይንህ ታያለህ እንደማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ሃዲዝ እንዲህ ይላል፡- “ጃሪር እብን አብዱላ (የአላህ ረሃማት በእሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፡- የአላህ መልዕክተኛ ሙሉ ጨረቃን ተመልክተው እንዲህ ሲሉ ከአጠገባቸው ነበርን - ልክ ይህችን ጨረቃ እንደምትመለከቱ ሁሉ በመጨረሻይቱ ዓለም የጌታችሁን ፊት ታያላችሁ፤ እርሱን በማየታችሁም ስሜታችሁ በፍጹም አይጎረብጣችሁም” (ሳሂህ ቡኻሪ እና ሳሂህ ሙስሊም)፡፡
አላህ ዛሬም በህልምና በራእይ ይናገራል፡፡ የእነዚህን ሕልሞች ትክክለኛ ትርጉም ስንረዳ እንደ ፈቃዱ መኖር እንችላለን፡፡ አሁኑኑ እየተናገረዎት ሊሆን ይችላል፡፡ ምላሽዎት ምንድነው? የህልምዎትን ምንነትና ዓላማ ለመረዳት መጣር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እኛ ደግሞ አላህ የሰጠዎትን ህልም እንዲረዱ ልንደግፍዎት ዝግጁ ነን፡፡