በአህምሮዎቻችን የሚፈጠሩ ሃሳቦች ምንጮቻቸው ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም - እኛው ራሳችን፣ አላህና፣ ጠላት (ሽይጣን) ናቸው፡፡ ሕልሞችም ተመሳሳይ ምንጮች አሏቸው፡፡
- • ከጠላት የሚላኩ ሕልሞች ፍርሃት አዘል ናቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ በጨለማ፣ በተስፋ ቢስነት እና በፈተና የተሞሉ ናቸው፡፡ ቅዠት የዚህ ግልጽ ምሳሌ ነው፡፡ አላህ ሊሆኑ ስላሉ መጥፎ ነገሮች ሊያሳይህ ወይም ሊነግርህ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሁል ጊዜ በእንደዚህ አይነት ህልም ውስጥ የተስፋ መልዕክት አለ፡፡አላህ ፍርሃትን በህይወት/ሽ አይጨምርም፡፡ ሁል ጊዜ ፍርሃትን ይቀንሳል፡፡ ምናልባት የፍርሃትህን መንስኤና መፍትሔውንም ይነግርሃል/ሻል፡፡
- • ከራሳችን የሚመነጩ ሕልሞች ደግሞ በህይወታችን ሆነው ባለፉ ክስተቶችና ጉዳቶች ዙሪያ ያጠነጥናል፤ ወይም በአካባቢያችን ለሚከሰቱ ነገሮች የሚሰጥ ምላሽ ይሆናሉ፡፡ በህይወታችን ያሉንን ፍላጎቶችና ፍርሃቶች የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አንድ ሰው የአንድን ሕልም ትርጉም ለመረዳት ስምንት ጥያቄዎችን አስቀመጠ፡-:
- • በህልሙ ውስጥ የሚታየው ስሜት ምንድነው? ሕልሙ ስለምንድነው የሚለውን ለመረዳት ዋናው ፍንጭ ሕልሙ ያዘለው ስሜት ነው፡፡ ፈርተህ ነበር? ድፍረት ነበረህ? ስሜቱን የፈጠረው ምንድነው?
- • ይህ ሕልም ስለትናንትናው የሚያስታውስህ ነገር አለ? እንደዚያ ከሆነ ሕልሙ ካለፈ ነገር ጋር የተያያዘ ነው፡፡
- • ሕልሙን ስታይ የት የነበርክ ይመስልሃል/ሻል? ቦታው ምን ያስታውስሃል? ለየት ያለ ትርጉም የሚሰጥህ ቦታ ነው? ያን ቦታ በሕልም ስታይ ምን ስሜት ፈጠረብሽ? ደህንነትና ፍቅር እንዲሰማህ የሚያደርግ ቦታ ነው ወይስ አደገኛና አስፈሪ ቦታ ነው?
- • ሕልሙን በአጭሩ ልትገልጽ ትችላለህ? ሕልሙ ትርጉም እንዲሰጥ በማለት አስተካክለህ ለመናገር አትሞክር!
- • ዋና ተዋናዮቹ ላይ አተኩር/ሪ፡፡ ማንን ያስታውሱሻል? ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ? በዚያ ሰው ውስጥ አንተነትህን ምን ያክል ታያለህ? ሕልሙ ስላንተ እንጂ ስለ ሌላ ሰው ስላልሆነ ሕልሙን በሌላ ሰው ላይ ለመለጠፍ አትሞክር፡፡
- • ሌላ ነገርን የሚወክል ምልክት (symbolism) ስለ መኖር አለመኖሩ ልብ ብለህ አስተውል፡፡ ያ ምልክት ምንን እንደሚወክል የምታውቀው ነገር አለ?
- • ይህ የግል እድገትህን በምን መልኩ ይነካል?
- • ሕልሙ ከመንፈሳዊ ሕይወትህ የቱን የሚነካ ይመስልሃል?
አንድ ሕልም ከአላህ የመጣ ከሆነ፡-
- • ከመጽሐፍ ቅዱስ (ክታበል-ሙቀደስ) ጋር ይስማማል፡- መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስት ጠሪነትን ይቃወማል፡፡ ይህም ጥንቆላንና መተትን ይጨምራል (ተውራት ዘሌዋዉያን 19፡31)፡፡ አላህ ምልክቶችን የሚጠቀም ከሆነ ላንተ ባላቸው ትርጉም ላይ በመመርኮዝ ይጠቀምባቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምልክቶች በአብዛኛው ከአላህ የተላከን ህልም ይወክላሉ፡፡
- • የአላህን ባህሪ የተላበሰና ከማንነቱ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፡፡ “እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” (2ጢሞቴስ 1፡7)፡፡
- • እውነተኛና ትክክል መሆን አለበት
- • መልካም ፍሬ የሚያፈራ መሆን አለበት፡- “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት ፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው” (ኢንጂል ገላትያ 5፡22-23)፡፡
- • ወደ አላህ የሚጠቁም መሆን አለበት፡፡ በተውራት ዘዳግም 13 እና 18 ውስጥ አላህ ትክክለኛና ሐሰተኛ መገለጦችን የምንለይባቸውን ቁልፍ ነጥቦች ያስቀምጣል፡፡
- • በቀለምና በብርሃን የተሽቆጠቆጠ ነው፡፡ ከአላህ የተሰጡ ሕልሞች በብርሃን፣ በቀለም ያሸበረቀ፣ ተስፋን የሚሰጥ፣ ሰላምና አድናቆትን የተላበሰ፣ እና የአላህን ባህሪ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡