ህልሞች ጠቃሚ የሆኑ እይታዎችን ይሰጣሉ፡፡ በቁርዓን ውስጥ ከተጠቀሱት ህልሞች መካከል ጥቂቱን ለአብነት ያህል ከነትርጉሞቻቸው እንዲህ እናቀርባለን፡፡

የነብዩ ዩሱፍ ህልሞች (ሱረቱ ዩሱፍ 12)፡- ነብዩ ዩሱፍ ሁለት ህልሞችን አለመ፡፡ በህልሞቹም ፀሐይ፣ ጨረቃና አሥራ አንድ ከዋክብት ሲሰግዱለት አየ፡፡ እነዚህ ህልሞች ከአላህ የተላኩ መለኮታዊ መልዕክቶች ነበሩ፡፡ ነብዩ ዩሱፍ ለወደፊት መሪ እንደሚሆንና ቤተሰቡም እንዴት ሊያከብሩት እንዳለ የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡

የነብዩ ኢብራሂም ህልም (ሱረቱ አልሰፋት 37)፡- ነብዩ ኢብራሂም በህልሙ አላህን ለመታዘዝ ልጁን ሲሰዋ ተመለከተ፡፡ ህልሙ ነብዩ ኢብራሂም ለአላህ ትዕዛዝ መታዘዝ አለመታዘዙን የሚፈትን የእምነት ፈተና ነበር፡፡ በመጨረሻም አላህ ልጁን በመስዋዕት በግ ታደገው፡፡ ይህ አላህን የመታዘዝና በእርሱ የመታመን አስፈላጊነትን ያመላክታል፡፡

የሁለቱ እስረኞች ህልም (ሱረቱ ዩሱፍ 12)፡- ነብዩ ዩሱፍ በእስር ቤት እያለ ሁለት ከእርሱ ጋር የታሰሩ ሰዎች - እነርሱም የንጉሡ ጠጅ አሰላፍና እንጀራ አቅራቢ ነበሩ - የተለያየ ህልም አለሙ፡፡ ነብዩ ዩሱፍ ህልማቸውን ተረጎመላቸው፡፡ ጠጅ አሰላፊው ወደ ሥራው እንደሚመለስና እንጀራ አቅራቢው ደግሞ እንደሚገደል ነበር፡፡ እነዚህ የህልም ፍቺዎች በኃላ ተፈጸሙ፡፡ ይሄም ነብዩ ዩሱፍ ህልም የመተርጎም ችሎታ እንዳለውና አላህም ነገሮችን እንደሚቆጣጠር ያመላክት ነበር፡፡

የፈርኦን ህልም (ሱረቱ ዩሱፍ 12)፡- የግብጹ ፈርኦን ሁለት ህልሞች አየ፡፡ በአንዱ ሰባት ወፋፍራም ላሞች በሰባት ከስታ ላሞች ሲዋጡ ተመለከተ፡፡ በሁለተኛው ደግሞ ሰባት አረንጓዴ የበቆሎ ራሶች በጠወለጉ ሰባት የበቆሎ ራሶች ሲዋጡ አየ፡፡ ነብዩ ዩሱፍ እነዚህን ህልሞች እንዲፈታ ተጠራ፡፡ እርሱም ሰባት የጥጋብ አመታት ከመጡ በኃላ ሎሎች ሰባት ክፉ የረሃብ አመታት እንደሚቀጥሉ የሚተነብዩ ህልሞች ናቸው አለ፡፡ ይህ የህልም ፍቺ ነብዩ ዩሱፍ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ በመሾም ሊመጡ ለነበሩት የረሃብ ዘመናት ዝግጅት እንዲያደርግ ዕድል ሰጠው፡፡

እነዚህ ምሳሌዎች በቁርዓን ውስጥ ህልም ያለውን ቦታና መለኮታዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እንደዚሁም ለሰዎች ምሪት በመሆን ያለውን ሚና ያመላክታል፡፡

More Stories
How to be Prepared
አማርኛ