ራሺድ እባላለሁ፡፡ በዓለም ላይ በእስልምና እምነት በጣም ጠንካራ ከሚባሉ ሃገሮች በአንዱ ተወለድኩ፡፡ ገና የአራት አመት ጨቅላ እያለሁ ህልም አየሁ፡፡ በህልሜም በሰፊው የአትክልት ሥፍራችን ውስጥ እመላለስ ነበር፡፡ አንድ ነጭ ልብስ የለበሰ እንግዳ ሰው ከፍራፍሬ ዛፎች ስር ስሜን ጠርቶኝ መልካም የወዳጅነት ስሜት አሳየኝ፡፡ ግርም ብሎኝ ለስለስ ያለ ንግግሩን እየሰማሁ ተጠጋሁት፡፡
“ራሺድ፤ እነዚህ ዛፎች ይታዩሃል?” አለኝ፡፡
“አዎን” ብዬ ወደዚህ ምስጢራዊ ሰው የበለጠ ተጠጋሁ፡፡
“የህይወታቸው ምንጭ ከዬት እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? እንዴት ነው ተራብተው ፍሬ የሚያፈሩት?” ሲል ጠየቀኝ፡፡
የንፋስ ሽውታው ቅጠሎቹን እያንቀሳቀሰ በሃሳብ ተመስጬ “አላውቅም” የሚል ምላሽ ሰጠሁት፡፡
“ና ላሳይህ” ብሎኝ ቀደም ሲል ወደማይታየኝና ወደዛፎቹ የሚፈሰውን ምንጭ ሊያሳየሰኝ ከዛፎቹ ጀርባ ወሰደኝ፡፡ ወደ ምንጩ በእርጋታ እየጠቆመኝ “ራሺድ፣ ውሃው ይታያሃል?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ “ይህ ውሃ በዛፎቹ ውስጥ ህይወት ይዘራል” አለኝ፡፡ ሰውዬው ውሃው እንዴት የዛፎቹን ስሮች በመመገብ ዛፎቹን እንደሚያኖር እየነገረኝ ያለውሃው ዛፎቹ እንደሚጠወልጉ በማስረገጥ አስረዳኝ፡፡ ፍሬዎቹ እንዴት እንደሚፈሩ የሚዘረዝር ውስብስብ ሂደቶቹን አስረዳኝ፡፡
ንግግሩን እያሰላሰልኩ እያለሁ ትኩረቱን ከዛፎቹ ወደ እኔ ሲመልስ አየሁ፡፡ በእርጋታና ፍቅር በተሞላው ድምፁ “ራሺድ፤ ልክ እንደዚህ ውሃ ልጠቀምብህ እፈልጋለሁ፡፡ ለሰዎች ህይወት እንድትሰጥ ልጠቀምብህ እፈልጋለሁ” ካለኝ በኃላ በቅጽበት ተሰወረ፡፡
“እማ፣ እማ፣ ፈጥነሽ ነይ” ብዬ እየተጣረሁ ወደ ቤታችን በር ሮጥኩ፡፡ እናቴ በድንጋጤ ከቤት ውስጥ ብቅ አለች፡፡ ከዚያም ነጭ ልብስ ከለበሰው ምስጢራው ሰውዬ ጋር የነበረኝን ቆይታ በጉጉት ነገርኳት፡፡
ጠንካራ መንፈሳዊ ሙስሊም የሆነችው እናቴ በነገርኳት ነገር ስለተነካች ለየት ያለ ምሪት እንዳገኝ በሰፈራችን ወዳለው መስኪድ ወሰደችኝ፡፡ ነጭ ልብስ የለበሰው ሰው በእድገቴ ጊዜ ሁሉ ጉብኝቱ ቀጠለ፡፡ ሳላቋርጥ መስኪድ በታማኝነት የምሄድ ብሆንም፤ እዛ የምማረው ትምህርት ነጭ የለበሰው ሰው በአትክልቱ ሥፍራ ከሚያስተምረኝ ጥልቅ ትምህርት ጋር ከፍተኛ ተቃርኖ ስላለው ግራ ተጋባሁ፡፡
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከመስኪድ ተለየሁ፡፡ ስለ አላህ እውነቱን የማወቅ ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ይህ ጉጉቴ ወደ ኢንጂል መራኝ፡፡ ይህም ነጭ ልብስ የለበሰው ሰው የሚያስተምረውን ትምህርት እንድከተል አደረገኝ፡፡ ኢንጂል በማጥናትና ኢሳ (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ለጠራቸው ሰዎች የአላህን ቃል በማካፈል እተጋለሁ፡፡
እኔና ነጭ ልብስ የለበሰው ሰው የተገናኛቸው ሰዎች ጥሪውን እንድንከተል እንዲፀልዩልን በትህትና እጠይቅዎታለሁ፡፡