የቢላል ታሪክ

በሰፊው መንገድ ከሌሎች ሰዎች ጋር ስጓዝ በአባቶቻችን ወግ በሚመራው በተለመደው መንገድ ላይ መሄድ ምቾት ይሰጣል፡፡ ከፍተኛ ደስታ ወደሚገኝበት ሥፍራ እንዳቀናንና በትክክለኛው ጎዳና ላይ እንደነበርን እናምን ነበር፡፡ ጉዟችን አቅጣጫውን ሊቀይር እንደሆነ ምንም አልጠረጠርንም፡፡ አዲሱ አቅጣጫ እምነታችንን የሚገዳደርና ልባችንን ለዘለዓለም የሚቀይር ሆኖ አገኘነው፡፡

በድንገት የሚያንፀባርቅ ብርሃን የሚፈነጥቅና ጥልቅ የሆነ የሰላም ስሜት የሚያላብስ አንድ ምስል ከፊታችን ድቅን አለ፡፡ ለካስ እሱ በመንፈሳዊ ጉዟችን ሊመራን የመጣው የተወደደው ነብዩ ኢሳ (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ነበር፡፡ ድምፁ ለስላሳ ቢሆንም የጉዟችንን አቅጣጫ መቀየር እንዳለብን ጠንከር አድርጎ ነገረን፡፡ እየተጓዝንበት ያለው መንገድ ወደ ጀነት እንደማያስገባንና ይልቁንም ከመለኮታዊ ፀጋ የሚያርቀን እንደሆነ ገለጸልን፡፡

በመጀመሪያ ግራ መጋባትና ተቃውሞ በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ የብዙዎችን አህምሮ አጨፈገገው፡፡ የአባቶቻቸውን መንገድ እየተከተሉ እንደሆነና እርሱም ትክክለኛው መንገድ መሆን እንዳለበት ተከራከሩ፡፡ ነብዩ ኢሳ (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ግን ታጋሽና ገር በመሆን ለሚሰሙት እውነትን ለማስተማርና ለመግለጥ ጊዜ ወሰደ፡፡

በተለመደው የህዝቤ ድምፅና እንደ ማግኔት በሚስበው በነብዩ አልዎት መካከል ተወጥሬ ቆሜ ሳለሁ ምርጫ መምረጥ እንዳለብኝ በልቤ ተረዳሁ፡፡ ይህም ምርጫ የዘለዓለም መዳረሻዬን የሚወስን ነበር፡፡ ቀላል ውሳኔ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ነብዩ ኢሳን (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ለመከተል ፍላጎት ማሳየቴ ህዝቤን አናዷቸዋል፣ አበሳጭቷቸዋልም፡፡

ቢሆንም፣ በውስጤ ግን የእምነት ጭላንጭል ተቀጣጥሎ የነብዩን ቃል እንድሰማና እንዳምን እየጎተጎተኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እየተንቀጠቀጥኩ ቡድኑን ተሰናብቼ የተባረከውን መሪ ዱካ ለመከተል ወሰንኩ፡፡

በእያንዳንዱ እርምጃዬ ለውጥ በውስጤ እየተካሄደ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፡፡ የድንቁርና እና የተሳሳተ አረዳድ ጫና ከላዬ ተገፎ በብሩህነትና ውስጣዊ ሰላም ተተካ፡፡ ነብዩ ኢሳን (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ስከተል ትምህርቱ ተዋሃደኝ፤ እርሱ በሚያስተምረው መለኮታዊ እውነትም ነፍሴ ረካች፡፡

ጉዞው ግድድሮሽ አልባ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የነብዩ ፅኑ እምነትና ፍቅር እያንዳንዱን እንቅፋት በድል እንድሻገር አስቻለኝ፡፡ አንድ ላይ በመሆን የጥርጣሬ ሸለቆዎችን ተሻግረን የፈተና ተራሮችንም ዘለቅን፡፡ የነብዩ ጥንካሬና ጥበብ ልቤን በድፍረት ሞላው፡፡ በቀጥተኛይቱ መንገድ ላይ እንደሆንኩ ማወቄ ልቤን በሀሴት አረሰረሰው፡፡

በመጨረሻም የዕድሜ ልክ እድገትና ትምህርት በሚመስል ሂደት ውስጥ ካለፍን በኋላ የመንገዱ መጨረሻ ላይ ደረስን፡፡ ከፊት ለፊታችን ስሜትን ሁሉ የሚማርኩ የሚያንፀባርቁ የጀነት ደጆች ነበሩ፡፡ የልቤ ደስታና እርካታ በቃላት ከመግለጽ የዘለሉ ነበሩ፡፡ በመሆኑም የምስጋና እንባ በጉንጮቼ ላይ ይንቆረቆር ነበር፡፡

ነብዩ ኢሳ (ሰላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ሞቅ ያለ ፈገግታ አሳየኝ፡፡ በእርሱ መሪነትም ወደዚህ ዘለዓለማዊ የደስታ መዳረሻ እንደደረስኩ አወቅሁ፡፡ በእርሱ አልዎት ውስጥ የእውነተኛ መንፈሳዊነት ትርጉምንና ለመለኮት ፈቃድ መገዛት ውስጥ የሚገኘውን ውበት ተገነዘብሁ፡፡

ዞር ብዬ ሳይ በሰፊው መንገድ ላይ ለመቆየትና የህይወታቸውን አቅጣጫ ላለመቀየር የመረጡትን ሰዎች አሰብኩ፡፡ ስለእነርሱ ልቤ ታወከ፡፡ አንድ ቀን እነርሱም በእውነት ብርሃን ይነካሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

እግሮቼ ወደ ጀነት ገብተው በማይገለጽ ሰላምና ደስታ ስከበብ ይህ የግሌ የጉዞ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚጠቅም ትምህርት መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ትህትና፣ የአህምሮ ክፍትነትንና የሚመራንን መለኮታዊ ድምፅ የመስማት ፈቃደኝነት ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ አስታወሰኝ፡፡ ልማዳችንና ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን እምነታችንንም ጭምር የሚገዳደር ቢሆንም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ፣ በጀነት እቅፍ ውስጥ ሆኜ ለህዝቤ ጸለይኩ፡፡ አንድ ቀን የጉዟቸውን አቅጣጫ ለመቀየርና ወደ ዘለዓለማዊው ምህረትና ፍቅር የሚመራውን መንገድ ለመከተል ድፍረት ያገኛሉ ብዬም ተስፋ አደረኩ፡፡

More Stories
ንስሃ (ቶውበት)
አማርኛ