አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በእሻራ (በህልም) ማየት ከስጋት፣ ከህመም፣ እና ከበሽታ ነጻ የመውጣት መልካም ዜና ነው፡፡
አንድ ሰው የኢሳ አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) መወለድ በህልሙ ካየ፤ በአላህ ፈቃድ፤ መልካም ዜናን ወይም የሚያስደስት ክስተትን ይሰብካል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ከነአሥራ ሁለቱ ደረሳዎቹ የሚያይ ከሆነ በመልካም ወዳጅነት ወይም ህብረት የተባረከ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ደቀመዝሙሩ (ደረሳው) ለመሆንና እነርሱ የኖሩትን ህይወት እንድትኖር የቀረበልህ ጥሪ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልም መገለጥ ደህንነትን፣ እርጋታንና ዘላቂ ሰላምን የማግኘት ትንቢት ነው፡፡
አንድ ሰው ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልሙ ጭንቅላቱን ሲዳብስለት ወይም አካሉን በዘይት ወይም በውሃ ሲያብስለት ቢያይ ሰውዬው በሽተኛ ከሆነ ይፈወሳል፤ እሰረኛ ከሆነ ይፈታል፡፡ አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልሟ ጭንቅላቷን በእጆቹ ሲዳብስ ብታይ በቀላሉ፤ ያለድካም፣ ያለህመም፣ ያለመከራ ልጇን እንደምትገላገልና ልጇንም ለእርሱ እንድትቀድስለት የቀረበላት ጥሪ መሆኑን ያሳያል፡፡
ማንም ሰው ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ዳግም ሲመለስ ወይም ከሞት ሲነሳ በህልሙ ቢያየው ያ ሰው በሌላ ሃገር የሚኖር ከሆነ ወይም ተጓዥ ከሆነ ወደ ቤተሰቡና ወደ ሃገሩ እንደሚመለስ ያሳያል፡፡ ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ሞትን ድል እንዳደረገ፣ እንደዚሁም ወደ ሰማያዊ ጀነት እንደሚወስደን የገባልንን ቃል የሚያስረግጥ በጣም ወሳኝ ማረጋገጫ ነው፡፡
አንድ ሰው የሆነ ነገርን በልቡ ተመኝቶ ኢሳ አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልሙ ከፊት ለፊቱ ሲቀመጥ፣ ከእርሱ ጋር ሲቀመጥ፣ ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ቢያይ ያ ምኞቱ እንደሚፈጻም የሚያሳይ ሲሆን እንደዚሁም የእውነተኛ ፍቅር መግለጫም ነው፡፡
ማንም ሰው ኢሳ አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በእሻራ ቢያይ ይህ የቅንነቱና ለጋስነቱ ምልክት ነው፡፡ ኢሳ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) የሆነ ቃል ቢናገረው እውነትን ይናገራል፤ ምክንያቱም ኢሳ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) የአላህ ቃል ነው፡፡
ማንም ሰው ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልሙ ወደ ቤቱ ሲገባ ቢያይ ያ ሰው በዚህ ስፍራ በደህንነት፣ በእርጋታና በበረከት ይኖራል ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ከእንጀራው ሲቆርስ በህልሙ ቢያይ ያ ሰው ለህይወቱ ሁሉ የሚበቃው በቂ ነገር ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ኢሳ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ከእርሱ ጋር በማዕድ ሲበላ ቢያይ ድህነትን አያይም ወይም ምንም ነገር አይጎድልበትም ይባላል፡፡
እንደዚሁም ኢሳ አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) በህልም ማየት የሚፈፀም ቃልኪዳንን ያመላክታል፡፡ ማንም እርሱን በመስቀል ላይ ቢያየው ከስቃይ እንደሚያመልጥና ንፁህ የሆነውን ፍቅሩን እንደሚቀበልና ከሞትና ከሃጢያት እንደሚድን ያሳያል፡፡
በህልም መስቀልን ማየት በአጠቃላይ የርህራሄን ባህሪይ ያመላክታል፡፡ አደጋን፣ ክፋትን፣ ወይም ፍትወትን ማሸነፍን ያመላክታል፡፡ ምክንያቱም የህይወትህን ምኞት፣ ፍትወትና ክፋትን እየሰቀልክ እንደሆነ ስለሚያሳይ ነው፡፡ በህልምህ መስቀልን በደረትህ ላይ አንጠልጥለህ ብታይ ቅንነትህን፣ መሰጠትህንና ለሌሎች (ለወዳጆችህ፣ ለጓደኞችህና የቅርብ ሰዎችህ ለሆኑት) መስዋዕት ለመሆን ፈቃደኛ መሆንህን ያመላክታል፡፡
መስቀልን በእሻራ ማየት በጸጋና በእውነት የተሞላ የአዲስ ህይወት ጅማሮን የሚያበስር ነው፡፡ አንድ ሰው በህልም መስቀል ያለው የአንገት ሀብል ሲያበረክትልሽ ብታይ የችግርሽ መቋጫና የህይወትሽ መሰናክሎች ማብቂያ መድረሱን ያመላክታል፡፡ ራሱ ሲሰቀል ወይም በመስቀል ላይ ሲሰቃይ በህልም የሚያይ ሰው በህይወቱ/ቷ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ነገር እንደሚገጥመው/ማት ወይም በማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት፣ እና በህይወቱ የተሃድሶ አራማጆችን ጎዳና እንደሚከተል ያመላክታል፡፡