የናስርን ታሪክ

ስሜ ናስርን ይባላል፡፡ የኩርድ ወገን የሆንኩ ኢራናዊ ነኝ፡፡ የኢስልምና እምነቴን በታማኝነት እንድጠብቅ ተደርጌ ነው ያደግሁት፡፡ እንደ ጸሎት፣ ፆም፣ ዘካ መክፈልና ሃጅ መሄድን የመሳሰሉ የእምነቱን ሥርዓቶችንም እተገብር ነበር፡፡

ባለቤቴና እኔ ጥሩ ኑሮ እንኖር ነበር፡፡ ባለቤቴ ኩባንያና ሁለት ሸሪኮች ነበሩት፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ አንደኛው ሸሪኩ በባንክ ደብተሩ ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ቼክ ይጽፍ ነበር፡፡ ያ ደግሞ ብዙ ችግሮችን አስከተለብን፡፡ ከሰባት አመታት በፊት፣ እያየሉ ከመጡ ችግሮች የተነሳ እኔና ባለቤቴ ኢራንን ለቀን ወደ ቱርክ ለመሰደድ ተገደድን፡፡

በቱርክ ስንኖር ሁል ጊዜ በስጋትና በስደት እንኖር ነበር፡፡ ምክንያቱም የአገሬው ሕዝብ ስደተኞችን ስለሚንቁ መብታቸውን አይጠብቁላቸውም ነበር፡፡ እንደዚሁም ወደ ኢራን በጉልበት ይመልሱናል ብለን እንሰጋ ነበር፡፡ ከነዚህ ችግሮች የተነሳ ከቱርክ ወደ ሌላ አጎራባች አገር በድብቅ ለመሄድ ወስነን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መውጣት ያለውንም አደጋ ለመቀበል ተዘጋጀን፡፡ እንደ ቤተሰብ ሰላማዊ ወደሆነ ሃገር መድረስ የምንችለው በዚህ አይነት መልኩ ብቻ እንደሆነ ታየን፡፡

በኢስታንቡል አንድ ሆቴል ውስጥ ሳለን በድብቅ የሚያሻግረን ሰው በቅርብ ቀን ወደ ግሪክ እንደምንጓዝ ነገረን፡፡ ምን ይገጥመን ይሆን በማለት ስጋት ገባኝ፡፡ ባለስልጣኖች ከያዙንስ? ወንድና ሴት ልጆቼ እንዴት ይሆናሉ? እንደ እናት ልጆቼ ደህንነታቸው መጠበቁንና መከራና ስቃይ እንዳያገኛቸው እርግጠኛ መሆን አለብኝ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ ውሳኔ እንድንወስን አላህ እንዲረዳን ለመንኩት፡፡ 

በሚቀጥለው ንጋት ላይ በክፋት የተሞሉና ቢላ በሚሲሉ ሰዎች የተሞላ ጠባብ መንገድ ላይ እንዳለሁ አለምኩ፡፡ ከዚያም እንደ ጸሐይ ብርሃን ደማቅ የሆነ ብርሃን አየሁ፡፡ ምን እንደነበረ አላወቅሁም፡፡ ነገር ግን እስክደርስበት ድረስ ቀጥ ብዬ ወደ ብርሃኑ ሮጥኩኝ፡፡ ስደርስም ብሩህና መልካም ፊት የነበረው በመካከለኛ ዕድሜ ያለ ሰው ቁጭ ብሎ አየሁት፡፡ እየተጣደፍኩ ስለመንገዱ ጠየቅሁትና “መንገድ ጠፍቶኝ ነው” አልኩት፡፡

“አትፍሪ” አለኝ፡፡ ከዚያም መልካሚቱን እጁን በራሴ ላይ ጫነብኝ፡፡ “አትፍሪ” ብሎ ሁለት ጊዜ ሲናገረኝ መላ ሰውነቴ በማልገልጸው መረጋጋት ተሞላ፡፡

“እዚህ ማንም የለኝም፤ ታዲያ እንዴት አልፈራም” አልኩት፡፡

“እኔ አረጋጋሻለሁ” ሲል መለሰልኝ፡፡ እሱ ከውስጤ የሚበራ መብራት ዓይነት መሰለ፡፡ ከዚያም መጽሐፍ ሰጠኝና “ይህ መጽሐፍ መንገድና እውነት ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ ተከተይ” አለኝ፡፡ መጽሐፉን ስከፍት ኢንጂል (ወንጌል) ነበር፡፡ ዘወር ብዬ ከኋላዬ ስመለከት ጸጥ ያለና ሰላማዊ መንገድ አየሁ፡፡ ከዚያም ነቃሁ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኛ ከመጣንበት ከተማ ከኢራን የመጣ በዚያው በቱርክ ሃገር የሚኖር የኩርድ ወገን የሆነ አንድ አማኝ መሆሩ ትዝ አለኝ፡፡ ለጥቂት አመታት ጎረቤታሞች ነበርን፡፡ እርሱና ቤተሰቡ በጣም መንፈሳውያን ነበሩ፡፡ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ለመጠየቅና ምክር ከእነርሱ ለመጠየቅ እናምናቸው ነበር፡፡ ስልክ ደውዬለት ያን የኩርድ ወገን አማኝ ስለሕልሜ ጠየቅሁት፡፡ ውብ የሆነ ትርጉም ሰጠኝ፡፡ አላህ ለእኔና ለቤተሰቤ ያለውን ፈቃድ ለመረዳት እንጂል (ወንጌል) ከእርሱ መውሰድ እፈልግ እንደሆነም ጠየቀኝ፡፡ በደስታ ተቀበልኩት፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት አመታት እየተመላለሰ የአላህን ፈቃድ እያስተማረን በኢሳ አል-መሲህ በኩል አላህ የገለጸልንን ፍቅር አስረዳን፡፡ ከዚያም ቤተሰባችን ለመጠመቅ ወሰነ፡፡ መንፈሳዊ አባታችን በነበረው ከኩርድ ወገን በሆነው ወዳጃችን መጠመቅ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡ አሁን ጌታንና ቤተክርስቲያንን እናገለግላለን፡፡

ያካፈልኳችሁ ሁሉ የፍቅር ውጤቶች ናቸው፡፡ አላህ ሕልም ላከልኝ፡፡ የአላህ ታማኝ ተከታይ ሕልሜን እንድገነዘብ ረዳኝ፡፡ እኔና ቤተሰቤም አላህ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የበለጠ እንድንረዳ አገዘን፡፡ አላህን የማወቅ ጉጉታችንና ለአላህ ያለን ፍቅር እንዲያድግ፣ እንደዚሁም ሌሎች በእኛ በኩል እርሱን እንዲያውቁና ወደ መንግስቱ እንዲቀላቀሉ እባክዎትን በተከታታይ ይጸልይልን፡፡

More Stories
የሙስጠፋ ታሪክ
አማርኛ