ስሜ አህመድ ነው፡፡ ከኢራቅ የመጣሁ የሺአ ኢስልምና ተከታይ ነኝ፡፡ ከአገሬ የወጣሁት በሳዳም ሁሴን ጊዜ ከነበረው ጦርነትና ማዕቀብ የተነሳ ነበር፡፡ መንግሥት ሊገለኝ ስለሚችል ተመልሼ ወደ አገሬ አልሄድኩም፡፡ ሁሉም የቤተሰቦቼ አባላት በጦርነቱ አልቀዋል፡፡ ወንድሞቼ በኢራንና በኢራቅ ጦርነት ጊዜ ሞቱ፤ ወላጆቼ ደግሞ በ2003 በሁለተኛው የኢራቅ ጦርነት ጊዜ ሞቱ፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በዮርዳኖስ አገር ነው የኖርኩት፡፡

አንድ ቀን መንገድ ላይ ቁልቁል እየሄድኩ ከልቤ ጋር እታገል ነበር፡፡ ለምንድነው ይህ ሁሉ የደረሰብኝ? ለምንድነው ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብኝና ቤተሰቦቼን ያጣሁት? ለምንድነው የስደተኛ ወረቀቴ የዘገየብኝ? ከራሴ ጋር አወራ ነበር፡፡ አንድ ቤተክርስቲያን ጋር እያለፍኩ ሳለሁ የሆነ ነገር አቆሜኝና ወደ ውስጥ እንድገባ ገፋፋኝ፡፡ ከዚህ በፊት ወደዚያ ቤተክርስቲያን ገብቼ አላውቅም፤ ስለዚህ ምቾት አልተሰማኝም፡፡ ወርውረው ያወጡኝ ይሆን? ነገር ግን ግፊቱን መቋቋም ስላልቻልኩ በዚያ ከሰዓት ወደ ቤተክርስቲያኑ ገባሁ፡፡

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ምንም ስዕላ ስዕሎች አልነበሩም፡፡ ሰዎች ቁጭ ብለው ሰባኪውን ይሰሙ ነበር፡፡ በእንግሊዘኛ ነበር የሚሰብከው፤ እንግሊዘኛዬ ደግሞ ጥሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዝም ብዬ ቁጭ ብዬ ለመረዳት ሞከርኩ፡፡ ሰባኪው የሚሰብከውን እንደማልረዳ የገባው ይመስላል፡፡ ስለዚህ ዋና ዋና ነጥቦቹን በአረብኛ መድገም ጀመረ፡፡ ያለውን ነገር በጣም ወደድኩኝ፡፡ ከፀሎት በኋላ ቀጥ ብሎ ወደ እኔ መጣና እንኳን ደህና መጣህ ሲለኝ ተደመምኩ፡፡ ተግባቢ ነበር፡፡ ከእርሱና ከቤተሰቡ ጋር ምሳ እንድበላ ጋበዘኝ፡፡ ከእርሱ ጋር እንድሄድ ስለጎተጎተኝ አብሬው ሄድኩ፡፡ ያ ለረጅም ጊዜ ወዳጅነት በር ከፈተልን፡፡

ፓስተሩን ጥያቄ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ በጣም ነበር የተረዳኝ፤ ጥያቄዎቼንም በፍቅር መለሰልኝ፡፡ ልገዳደረው ሞከርኩ፤ ነገር ግን በጣም የተረጋጋና የሚያምነውን የሚያውቅ ሰው ነበር፡፡ ቁርአንና መጽሐፍ ቅዱስን አብረን ማጥናት ጀመርን፡፡ ሁለቱንም ያዉቃቸዋል፡፡ ሁሉንም ነገር አወራን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተበረዘ መሆን አለመሆኑን፣ የኢሳን ማንነት፣ ስለ ስላሴ፣ የኢሳ በመስቀል ላይ ሞት፣ የቤተሰብ ጉዳዮች፣ የቁርዓንና የመጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ምሪት መጻፍ፣ የሐዲዝ ተዓማኒነት፣ እና የመሳሰሉትን አወራን፡፡ ነገሮችን ለየት ባለ መንገድ ማየት ጀመርኩ፡፡ ለአራት አመታት በጓደኝነትና በጥናት ከፓስተሩ ጋር ከቆየን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተበረዘ የአላህ ቃል መሆኑን ተቀበልኩ፡፡ ልክ ቁርዓን “(ከአላህ) ባለሟሎች የሆነ” (ሱረቱ አል-ኢምራን 3፡45) እንደሚለው የሱስን ለየት አድርጌ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን እርሱ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው ብዬ አልተቀበልኩትም ነበር፡፡

ትዝ ይለኛል አንድ ምሽት፣ ከወዳጄ ጋር ስለ የሱስ ማንነት ብዙ ከተወያየን በኋላ አላህ ስለማንነቱ ሙሉ እውነት እንዲገልጥልኝ ጸለየልኝ፡፡ ከዚያም ማወቅ ለሚፈልጉት ሁሉ አላህ እውነቱን እንደሚገልጥላቸው ነገረኝ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ንጋት ላይ ሕልም አለምኩ፡፡ በሕልሜም አንድ ነጭ የለበሰ ሰው እያነጋገረኝ ሳላ “ስለ ማንነቴ ለምን ትጠራጠራለህ?” በማለት ጠየቀኝ፡፡

እኔም፤ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ማነህ?” አልኩት፡፡

“እኔ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነኝ፡፡ ጓደኛህ የሚልህን ስማው፡፡ እውነቱን እየነገረህ ነው” አለኝ፡፡

ከጠዋቱ 11 ሠዓት ላይ ስነቃ ፓስተሩን ጓደኛዬን ደውዬ እንድነግረው መንፈሴ በጣም ይጎተጉተኝ ነበር ፡፡ ስልኩን ሲያነሳ “አምናለሁ!” አልኩት ከፍ ባለ ድምጽ፡፡

በግራ መጋባትና በእንቅልፍ ልቡ “ምንድነው የምታምነው?” አለኝ፡፡

“እየነገርኩህ ነው፤ አምናለሁ!” ብዬ የመጮኽ ያክል ነገርኩት፡፡ ምን ማለቴ እንደሆነ መረዳት አልቻለም፡፡ ስለ ሕልሜ እንዳልነገርኩት ሳላውቅ አራት ጊዜ ተመሳሳይ መልስ ሰጠሁት፡፡ በመጨረሻም “የሱስን በሕልሜ አየሁት” አልኩት፡፡ “አምላኬና አዳኜ እንደሆነ አምናለሁ!” አልኩት፡፡ ወዳጄ በጣም ደስ ብሎት ሙሉውን እውነት ስለገለጸልኝ የሱስን እያመሰገነ በስልክ ጸለየልኝ፡፡ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንዳስረክብም አበረታታኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚያ የጋራ ጸሎት ላይ በኢየሱስ ስም ጸለይኩኝ፡፡

ያን ቀን የመንፈስ ቅዱስን ውትወታ ሰምቼ ወደዚያ ቤተክርስቲያን ባልገባ፤ ወይም ፓስተሩ ከቤተሰቡ ጋር ምግብ እንድበላ ሲጋብዘኝ እምቢ ብል ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም፡፡ በእነዚያ አራት አመታት ውስጥ አላህ ብዙ ነገር እንድማር እንዴት እንደመራኝና እውነቱን በሕልሙ በልቤ ላይ እንዳተመልኝ አያለሁ፡፡ ቀላል ሕይወት አይደለም የምኖረው፤ ነገር ግን ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር “መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ” (2ጢሞቴዎስ 2፡12) በማለት ድምፄን ከፍ አድርጌ መናገር እችላለሁ።

More Stories
How to be Prepared
አማርኛ