ስሜ አሊ ነው፤20 ዓመቴ ነኝ፡፡ በፓኪስታን አገር እስልምናን ከፍ አድርገው በሚመለከቱ ቤተሰቦች መካከል ነው ያደኩኝ፡፡ እንደ አምስት አወቃት ሰላት፣ ዳአዋ መውጣት፣ መጾም፣ ደሃን መርዳት፣ ዘካን መክፈል የመሳሰሉትን የእምነቱን ሥርዓቶች እፈጽም ነበር፡፡ በኃይማኖቴ አክራሪ ነበርኩ፡፡ ከሃዲዎች ናቸው ብዬ ስለማምን ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እንኳን ፈቃደኛ አልነበርኩም፤ ምክንያቱም ከእነርሱ ጋር በመቀራረብ የዘለዓለም ሕይወት ማጣት አልፈልግም፡፡
ሁለት ሕልም አለምኩ፡፡ በሁለቱም ነጭ የለበሰ ሰው አየሁ፡፡ የመጀመሪያውን ሕልም ያለምኩት በስምነት ዓመቴ ነበር፡፡ በሕለሜ አላህን አየሁት፡፡ አላህ በጣም ብሩሁ በሆነ ነጭ ብርሃን ተገለጠልኝ፡፡ ፊቱን በግልጽ ማየት አልቻልኩም፡፡ ነገር ግን ረጅምና ነጭ ፂሙ ይታየኝ ነበር፡፡ ከዚያም አላህ ተናገረኝ፡፡ ምን እንደተናገረኝ ትዝ አይለኝም፤ ነገር ግን በፊቱ ሆኜ እንዴት ደስ እንዳለኝና በሰላም እንደተሞላሁ ትዝ ይለኛል፡፡ በዚያው ልክ ታላቅነቱ ተሰማኝ፡፡
ዕድሜዬ 18 አመት ሲሆን እንደገና ነጭ የለበሰ ሰው በህልም ተገለጠልኝ፡፡ በጦር ሜዳ ነበርን፡፡ እርሱ ከ10 ወይም ከ12 ሰዎች ጋር ሆኖ ብዙ ሠራዊት ከነበረው ዘንዶ ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ጦርነቱ አስከፊ ነበር፤ ነገር ግን ነጭ የለበሰው ሰውዬ በመጨረሻ ዘንዶውንና ጠላቶቹን አሸነፋቸው፡፡ እነርሱም ተጣሉ፡፡ ቁጭ ብዬ ከእርሱ ጋር ለመነጋገርና ከእርሱ ለመማር ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ከጉኑ በመሆነ ልገልጸው የማልችል ደስታ ተሰማኝ፡፡ ከዚህ በፊት ተለማምጄው የማላውቅ ሰላምና ደስታ ተሰማኝ፡፡
ከእንቅልፌ ስነቃ ሕልሜን መረዳት ፈለግሁ፡፡ ትርጉሙን ለማወቅ ብዙ ሰው ጠየቅሁ፤ ነገር ግን ማንም አጥጋቢ መልስ አልሰጠኝም፡፡ ኢንተርኔት መጎርጎር ጀመርኩ፤ ከዚያም በእናንተ በይነ-መረብ ላይ አላህን በሕልም ማየት እንደምንችል የሚናገር ጽሑፍ አነበብኩ፡፡ ነጭ የለበሰው ሰው ማነው? ዘንዶው ማነው? ለምንድነው የሚዋጉት? ለምንድነው ይህ ሕልም የተገለጠልኝ? ምን ማለትስ ነው? ብዬ መረጃ እንድትሰጡኝ ጻፍኩላችሁ፡፡
የላካችሁልኝ ምላሽ አስደናቂ ነበር፡፡ በሕልሜ ያየሁትን ነገር በትክክል የሚገልጹ የኢንጂል (የወንጌል) ጥቅሶችን ላካችሁልኝ፡፡ ተደመምኩ፡፡ “በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና መንግሥት፣ የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቷል። ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከስሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሏልና። እነርሱም በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሡት፤እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣ለነፍሳቸው አልሳሱም። ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል” (ራእይ 12፡7-12)፡፡
ጥቅሱን ካነበብኩ በኋላ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡ ይህ ኢንጂል ውስጥ አለ? የተበረዘ ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በሕልም ያየሁትን ግልጽ አድርጎ ተረከልኝ፡፡ ልገፋው አልቻልኩም፡፡ ነጭ ስለለበሰው ሰው ሁሉን ነገር ማወቅ ፈለግሁ፡፡
ነጭ ስለለበሰው ሰው ለማወቅ ቅርብ ጊዜ ነው ጉዞ የጀመርኩት፡፡ ማን ይሆን? ለምንድነው እንደዚህ ዓይነት ሕልም ያለምኩኝ? ዓይኖቼን ከፍቶልኝ እንዳጠናና የበለጠ እንዳውቅ ስላደረገኝ ስለ በይነ-መረባችሁ አመሰግናችኋለሁ፡፡