ስሜ ካዚም ይባላል፡፡ የሺአ እስልምናን ከሚከተሉ የኢራቅ ቤተሰቦች የተወለድኩ ሰው ነኝ፡፡ አገሬን ያጠፋትን ጦርነት ማየት ሰለቸኝ፡፡ በሺአ እና ሱኒ ሙስሊሞች መካከል ካለው ጥላቻ የተነሳ ሕዝቤ በየቀኑ ሲሞት አይቼአለሁ፡፡ ሕይወት መከራ ነበር፡፡ አጥፍቶ ጠፊ ይገለኛል ብዬ ከፍተኛ ስጋት ነበረኝ፡፡ ለምንድነው በሰላም አብረን የማንኖረው? በማለት እገረም ነበር፡፡ ሁላችንም ሙስሊሞች ነን፡፡ አንድ እምነት አይደል ያለን? አንድ ቁርአን አይደለም የምናነበው? አንድ “ቀጥተኛ መንገድ” አይደለም የምንከተለው?
የአባቴን፣ የአያቴንና የሌሎችም የቀደሙ አባቶቼን መንገድ ነበር የምከተለው፡፡ ቁርዓንን አነባለሁ፤ በረመዳን እጾማለሁ፤ አሹራን እጠብቃለሁ፤ እና የኢማሞችን ቀብር እጎበኛለሁ፡፡ መልካም የሺአ ሙስሊም ነበርኩ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮች እያስጨነቁኝና በጥያቄ እየሞሉኝ ነው፡፡ ለምንድነው አንዳንድ የቁርአን አያዎች (ቁጥሮች) ስለ ጥላቻ የሚናገሩት? ሰዎች ለመገዳደል እነርሱን እንደሰበብ እየወሰዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ሱረቱ አል ተውባ (ምዕራፍ 9)፡፡ እያለቀስኩ (እንደ ባህላችን ወንድ የማያለቅስ ቢሆንም) አላህን፡- ለምንድነው ይህን ጦርነት የማታስቆመው? እያልኩ እለምነው ነበር፡፡ ነገሮች ግን እየባሱ ሄዱ፤ በዚህን ጊዜ ቤተሰባችን ሃገር ለቅቆ ለመውጣት ወሰነ፡፡ ስለዚህ ወደ ዮርዳኖስ ሄድን፡፡ እዚያ ሰላም ነበር፡፡ አጥፍቶ ጠፊዎች አልነበሩም፤ ቦንብ እያፈነዱ ሕንፃዎችን የሚያጋዩ፣ መኪኖችንና ሰዎችን የሚበጣጥሱ መኪናዎች አልነበሩም፡፡
በአማን ከተማ ጂም (የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ) መሄድ ጀመርኩ፡፡ የተለያዩ ሰዎችን አገኘሁ፤ አንድ ሰው ግን ከሌሎች ለየት ያለ ነበር፡፡ ለሳምንታት ተከታተልኩት፡፡ የተረጋጋና ፈገግታ የማይለየው ሲሆን ሰዎችን ማበረታታት ይወዳል፡፡ ጓደኛ አደርገዋለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡ አነጋገርኩት፤ እርሱም በቅርብ በሚገኝ የኢራቅ ምግብ ቤት አብረን እንድንበላ ጋበዘኝ፡፡ የቤተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ የፈለገ ይመስላል፡፡ ከሌሎች ሰዎች እንዲህ እንዲለይ ያደረገው ምን እንደሆነ ማወቅ ፈለግሁኝ፡፡ የደስታውና የሰላሙ ምንጭ ምንድነው? ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎችን ጠየኩት፡፡ ምላሹ አስደነገጠኝ፡፡ የሱስ እንደሆነ ነገረኝ፤ በኢስልምና እንደምንጠራው “ነቢዩ ኢሳ አል-መሲህ ነው” አለኝ፡፡ ለሰዓታት ከቁርአንና ከክታበል ሙቀደስ (መጽሐፍ ቅዱስ) ስለ ኢሳ አካፈለኝ፡፡ ከእኔ በላይ ቁርአንን ያውቃል፡፡ ቀልቤን የሳበ ነገር ተናገረ፡- ቁርአንም ኢንጂልም ሰላም የሚሰጠው ኢሳ ነው ይላሉ አለኝ፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ተከራከርኩት፤ ነገር ግን እርሱ የተረጋጋና ወዳጅነትን የተላበሰ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር አልተከራከረም፡፡ ይልቁንም ከቁርአንና ከኢንጂል ጥቅስ (አያዎችን) እያወጣ ያሳየኝ ነበር፡፡
ቁርአን፣ ሐዲዝና ሌሎች የኢስልምና መጽሐፎችን ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ላይ እየፈለኩ፣ የተለቪዥን ፕሮግራሞችን፣ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን እየተከታተልኩ ለእርሱ የምሰጠውን መልስ መፈለግ ተያያዝኩኝ፡፡ ይህ ቁርአንን ለየት ባለ መልኩ እንዳነብ አደረገኝ፡፡ አእምሮዬ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ነበር፡፡ እርሱ የነገረኝን ኢሳ መውደድ ጀመርኩኝ፡፡ ኢሳ ለየት ያለ ነበር - አፍቃሪ፣ ሰዎችን የሚቀርብና ሰላማዊ ነበር፡፡ ነገር ግን አምላክ ነው ብዬ ማመን አቃተኝ፡፡ እንደዚህ ማመን አላህ ይቅር የማይለው ብቸኛው ሐጢያት የሆነው ሽርክ ነው፡፡
አንድ ቀን ሳልጠብቀው ለየት ያለ የኢንጂል መጽሐፍ ሰጠኝ፡፡ አንብበውና እንወያይበታለን አለኝ፡፡ በሕይወቴ ኪታበል ሙቀደስን (መጽሐፍ ቅዱስን) አይቼ አላውቅም ነበር፡፡ ፈራሁ፡፡ ለጓደኛዬ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ተቀበልኩት፤ ነገር ግን የማንበብ ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ ያን ምሽት ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት መጽሐፉን በመሳቢያ ውስጥ ሸሸግኩት፡፡
በዚያ ምሽት የሚያስገርም ሕልም አየሁ፡፡ በሕልሜም ነጭ ልብስ የለበሰና እንደ ፀሐይ የሚያበራ ሰው አየሁ፡፡ ወዳጄ የሰጠኝን መጽሐፍ እንዳነብ ነገረኝ፡፡ “አንተ ማነህ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡
እርሱም፤ “መጽሐፉን አንብበውና ማንነቴን ታውቃለህ” አለኝ፡፡
ልክ ከእንቅልፌ እንደነቃሁ መጽሐፉን ማንበብ ጀመርኩኝ፡፡ ወደድኩት፡፡ ማንበቤን ማቆም አቃተኝ፡፡ ማን በሕልሜ እንደተገለጠልኝም አወቅሁ፡፡ ጓደኛዬ ትክክል መሆኑን አወቅሁ፡፡ ኢሳን ማምለክ መጀመር እንዳለብኝ ተረዳሁ፡፡ በሕይወቴ የጎደለኝን አገኘሁ፡፡
ለኢሳ ያለኝ አዲስ ፍቅር ከቤተሰቤና ከወዳጆቼ ብዙ ችግር አስከተለብኝ፡፡ በዚያን ጊዜ ያ ጓደኛዬ በጣም ረዳኝ፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ቆይቼ በሕይወቴ እንድመሰክርላቸውና እኔ ያገኘሁትን እውነት እንዲያገኙ አበረታታኝ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታዬና አዳኜ መሆኑን አውቅሁ፡፡ በየቀኑ እወደዋለሁ፤ አወድሰዋለሁም፡፡ እርሱ በሕይወቴ ውስጥ ሳይኖር መኖር አልችልም፡፡ ወዳጄ የኢየሱስን ማንነት ለማሳየት የሚጠቀምባቸውን የሰላም፣ የደግነትና የፍቅር ዘዴዎችን በመጠቀም አሁንም ከቤተሰቦቼ ጋር እየኖርኩ ነኝ፡፡ እንዲያመልኩትና እንዲድኑ ኢሳ በሕልም እንዲገለጥላቸው እየጸለይኩ ነው፡፡ እባክዎትን ለእኔና ለቤተሰቦቼ ይጸልዩልኝ፡፡