ስሜ ጀምሲድ ነው፤ የአፍጋንስታን ተወላጅ ነኝ፡፡ ተወልጄ ያደኩት በጣም ኃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነበር፡፡ በአገሬ ያሉ አብዛኞቹ ቤተሰቦች እንደዚሁ ናቸው፡፡ ከድህነት የተነሳ ትምህርቴን ማጠናቀቅ አልቻልኩም፡፡ በአፍጋንሰታን አገር እንደሚገኙ ሌሎች ልጆች ሁሉ ገና ከልጅነቴ ቤተሰቦቼን ለመርዳት መስራት ጀመርኩ፡፡ ልክ እንደአብዛኛው የአፍጋን ወጣቶች በ19 ዓመቴ አገባሁ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አላህ በወንድ ልጅ ባረከን፡፡ ቀለል ያለ ሕይወት የምንኖር ብንሆንም ደስተኞች ነበርን፡፡
ልጄ ሁለት ዓመት ሲሆነው ልጄና ባለቤቴ ከአፍጋን ጎሳዎች በአንዱ ተጠለፉ፡፡ ለመፈለግ ሞከርኩኝ ግን አላገኘኃቸውም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የባለቤቴ ቤተሰቦች ልጃቸውን ካላገኘሁ እንደሚገሉኝ ይዝቱብኝ ጀመር፡፡ ገንዘብ፣ ሰዎችና መሳሪያ ስለሚያስፈልግ ይህን ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ከብዙ ዛቻ በኋላ በ2000 አገሬን ለቅቄ ለመውጣት ወሰንኩኝ፡፡ ከአገሬ ወጥቼ በብዙ የአጎራባች አገሮች ተዘዋወርኩ፡፡ ከብዙ ችግሮችና መከራዎች በኋላ ሶሪያ ገባሁ፡፡ እኔ አረብኛ ስለማልናገር እዛም አንዳንድ ችግሮች ገጠሙኝ፡፡ ለመኖር ሥራ ማግኘት ነበረብኝ፤ ነገር ግን ለብዙ ጊዜ ሥራ አጣሁኝ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአንድ ዳቦ መጋገሪያ ውስጥ ሥራ አገኘሁ፡፡ ማደርያዬም እዛው ነበር፡፡ የዳቦ መጋገሪያው ባለቤት ክርስቲያንና የሊባኖስ ዜጋ ነበር፡፡ በእኔ አመለካከት እርሱ ከሃዲ ነው፡፡ ለእርሱ መስራት አልፈለኩም፤ ነገር ግን ሥራ በጣም ያስፈልገኛል፡፡
ቀጣሪዬ ለእኔ መልካም ነበር፡፡ በጥሩ ሁኔታም ይዞኝ ነበር፡፡ ያ ደግሞ ይረብሸኝ ነበር፡፡ እንዴት እንደዚህ ያደርጋል? ሙስሊም አይደለም፡፡ እውነተኛውን አምላክ የማያውቅ ከሃዲ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን ልጠይቀው ወሰንኩኝ፡፡ “እኔ ስላንተና ስለኃይማኖትህ ምን እንደማስብ እያወቅህ ለምን በእንደዚህ መልካም አያያዝ ታስተናግደኛለህ?” አልኩት፡፡
እርሱም “ጠላቶቼን እንድወድ፣ ይቅርታ እንዳደርግላቸውና እንድጸልይላቸው ጌታ ያስተማረኝ ነገር ነው” ሲል መለሰልኝ፡፡
ምላሹ አስደነገጠኝ፡፡ በጣም ልቤን ነካኝ፡፡ ይህ ከሃዲ ብዬ ባየሁትና የኃይማኖቴ ተከታዮች በምላቸው ሰዎች መካከል ምን አይነት ልዩነት ነው ያለው! ይህ ሰው በጣም በተሻለ ሁኔታ አስተናገደኝ፡፡ እኛ ጠላት የምንላቸው ሰዎች መታረድ አለባቸው ስንል የዚህ ሰውዬ አምላክ ግን እንዴት ጠላቶቹን እንዲወድ ያስተምረዋል?
አንድ ቀን ቀጣሪዬ ከእርሱ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን እንድሄድ ጋበዘኝ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን እንድሄድ ስጋበዝ ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ መጀመሪያ አመነታሁ፤ በኋላ ግን እሞክራለሁ አልኩት፡፡ በሕይወቴ ወደ ቤተክርስቲያን ስገባ ይሄ የመጀመሪያ ነበር፡፡ ትንሽ ፈርቼ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎቹ የሚገርሙ ናቸው፡፡ በፈገግታና በደስታ ሰላምታ አቀረቡልኝ፡፡ አነዚያን ጊዜያት በጭራሽ አልረሳሁም፡፡
ቤተክርስቲየኑን ወድጄ ነበር፤ ነገር ግን ፍርሃትም ነበረኝ፡፡ የበለጠ ማወቅ ፈለግሁ፡፡ ለምንድነው እንደዚህ ልዩ የሆኑት? የደስታቸውና የሰላማቸው ምስጢር ምንድነበር? በእኔና በእነርሱ መካከል ልዩነት የፈጠረው ምንድነው?
እንደስደተኛ ተመዘገብኩ፤ በደማስቆ የነበረውን የተ.መ.ድ. ቢሮንም እጎበኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን ለስደተኞች ቤተሰቦች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚል ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ልመዘገብ ወሰንኩኝ፤ ነገር ግን ምን እያደረኩ እንደሆነ የሚያውቅ ሰው ይኖር ይሆናል ብዬ ፈራሁ፡፡ ተጨነቅሁ፣ ግራ ተጋባሁ፤ መተኛትም አልቻልኩም፡፡ ውሳኔ መወሰን እንዳለብኝ አውቅ ነበር፡፡
አላህ በግራ መጋባት መካከል አይተወንም፡፡ ከሁለት ቀን የውስጥ ትግል በኋላ ተኝቼ “አትፍራ” የሚል ድምጽ ሰማሁ፡፡ ድምጹ ምቾትና ሰላም እንዲሰማኝ አደረገኝ፡፡ ነቃሁ፤ በክፍሉ ውስጥ ማንም አልነበረም፡፡ በሚቀጥለውም ቀን “አትፍራ” የሚል ተመሳሳይ ድምጽ ሰማሁ፡፡ በማግስቱ ስነቃ ለማመን የሚያስቸግር የሰላም ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ በመጨረሻም ፍርሃቴ ጠፋ፡፡ ፍርሃትንና ግራ መጋባትን የሚያስወግድ ድምጽ እንዴት ደስ ይላል! እንዳልፈራና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ እንድሳተፍ ሊያበረታታኝ ወደ እኔ የመጣ የአላህ ቃል መሆኑ ገባኝ፡፡
አንድ ቀን የተ.መ.ድን ቢሮ ለመጎብኘት ስሄድ በዛ ያሉ ሰዎች በማስታወቂያ ቦታ ላይ ቆመው አየሁ፡፡ አንደኛው ማስታወቂያ አረብኛ መማር ለሚፈልጉ የወጣ ነበር፡፡ እነዚህን ትምህርቶች ለመጀመር ቢያንስ ሶስት ሰዎች መመዝገብ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ሌሎች ሰዎች አረብኛ ለመማር ፍላጎት አይኖራቸውም ብዬ ሰጋሁ፡፡ ነገር ግን የአላህ መንገዶች ከእኛ መንገዶች ይለያሉ፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሌሎች ትምህርቱን መማር የሚፈልጉ ሰዎች እንደተገኙ ከተ.መ.ድ. ቢሮ ተደውሎ ተነገረኝ፡፡ ስለዚህ የአረብኛ ትምህርት መዝገባ ክፍት ሆነ፤ ትምህርቱም የሚሰጠው ሐሙስ ሐሙስ ነው፡፡
ከኑሮ ሁኔታችን የተነሳ ትምህርት ቤት መግባት አልቻልኩም ነበር፤ ነገር ግን አላህ መንገዶች አስደናቂ ናቸው፡፡ የአላህን ቃል እንዳሰላስልና ቃሉንም እንድሰማ የሚረዳኝን ሰው አላህ ላከልኝ፡፡ በደስታ ፈነደቅሁ፤ በዚያው ሰውዬ በኩል በቋንቋዬ ማንበብና መጻፍ ተለማመድኩ፡፡ ይህ ከአላህ የተላከ ተዓምር ነበር፡፡
በየእለቱ የጌታ ኢየሱስ ማንነትን በማወቅ አድጋለሁ፤ አዳኜና የህይወቴ ጌታ መሆኑንም እቀበላለሁ፡፡ ከጌታ የሱስ ጋር የሚኖር ኑሮ በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ከባድ ሁኔታዎችንም ጨምሮ በሁሉም ነገር ጌታ ከእኔ ጋር መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ጸሎቴ እርስዎም የሱስን የግል አዳኝዎ አድርገው እንዲቀበሉት ነው፡፡