ስለ ሕልም ብዙ ሐዲዞች አሉ፡፡ እንደዚሁም የታወቀው የነቢዩ ዩሱፍ ታሪክም በቁርአን ውስጥ ይገኛል፡፡
“የጻድቅ ሰው መልካም ሕልም (የሚፈጸም) ከአርባ ስድስት የነቢይነት ክፍሎች አንዱ ነው” (ሰሂህ ቡኻሪ)፡፡ ሌላ ሐዲዝ እንዲህ ይላል፤ “መልካምና እውነተኛ ሕልም ከአላህ ነው፡፡ መጥፎ ሕልም ደግሞ ከሸይጧን ነው” ((ሰሂህ ቡኻሪ)፡፡
በኢስላም ሦስት አይነት ህልሞች አሉ፡-
“ሦስት ዓይነት ሕልሞች አሉ፡- ከአላህ የተሰጠ ሕልም፣ ከሰይጣን የሚላክ የሚያስጨንቅ ሕልም፣ እና ነቅቶ እያለ ሰው አስቦት ከነበረው በእንቅልፍ ልቡ የሚያያቸው ሕልሞች ናቸው” (ሰሂህ ቡኻሪ 6499፤ ሰሂህ ሙስሊም 4200)፡፡
- • ራህመኒ፡- ረሃመቱ ብዙ ከሆነው ከአላህ የተላከ እውነተኝ ሕልም ነው፡፡
- • ነፍሰኒ፡- ከግል ፍላጎት የሚመነጭ ሕልም
- • ሸይታኒ፡- ከሰይጣን የሚላክ ሕልም
አል-ሙሐላብ እንዲህ ይላል፡- “አብዛኞቹ የጻድቅ ሰው ሕልሞች መልካም ሕልሞች ናቸው፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ጻድቅ ሰውም ትርጉም የለሽ ሕልም ሊያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚከሰተው በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን በእነርሱ ላይ ያለው ቁጥጥር በጣም ደካማ ነው፡፡ ለሌሎች ሰዎች ደግሞ የተገላብጦሽ ነው፤ ምክንያቱም ሰይጣን እነርሱን አጥብቆ ይዟቸዋል፡፡”
ስለዚህ፤ አዎን አላህ በሕልምና በመገለጥ ለሰዎች ያናገራል፡፡ “ሰው ባያስተውለውም እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል፤ ሰዎች አልጋቸው ላይ ተኝተው ሳሉ ከባድ እንቅልፍ ሲወድቅባቸው በሕልም፣ በሌሊትም ራዕይ፣ ይናገራል፡፡ በጆሯቸው ይናገራል፤ በማስጠንቀቂያ ያስደነግጣቸዋል፤ ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሳል፤ ከትዕቢት ይጠብቃል፤ ነፍሱን ከጉድጓድ ሕይወቱንም ከሰይፍ ያድናል” (ተውራት ኢዮብ 33፡14-18)፡፡
ስለዚህ ከላይ በተጻፈው ጥቅስ መሠረት አላህ በሕልም ከታች ለተዘረዘሩት ምክንያቶች ይናገራል፡-
1. ክፉ ከመስራት ሰዎችን ለመመለስ
2. ሰዎችን ከትዕቢት ለመጠበቅ
3. ሰዎችን በትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት
4. ሰዎችን ከሞት ለመጠበቅ
አላህ በሕልም የሚናገረን ቢሆንም፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ወሳኝ መርሆዎችን ይነግረናል፡-
- • ሕልምህን መርምር፡- “ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ” (መክብብ 5፡7)፡፡ ይህ ጥቅስ ከመጠን በላይ በህልም ላይ ከመደገፍ ያስጠነቅቃል፡፡ አብዛኛውን ትኩረታችንን በሕልም ላይ ማድረግ የለብንም፡፡ ይልቁንስ አላህ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል የሚናገረንን ልብ ብለን ለማዳመጥ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡
- • የሕልሙን ምንጭ መርምር፡- “የእሥራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኃል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር (ኤርሚያስ 29፡8-9)፡፡ ይህ ጥቅስ እምነታችንን ሰዎች በሚያልሙት ሕልም ላይ እንዳናደርግ ያስጠነቅቀናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሐሰተኛ ነቢያቶች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳት ያላለሙትን ሕልም አለምን ብለው ይናገራሉ፡፡ ማንም ሰው ስለ ሕልም ሲያወራ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፤ የሚሉትንም ነገር ሁሉ ከክታብ አል-ሙቀድስ (ከመጽሐፍ ቅዱስ) እይታ አንጻር መመርመር አለብን፡፡