የነቢዩ ዳንኤል ራእይ - በዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 7

ታሪኮችን፣ ትንቢቶችንና ራእዮችን በያዘው የነቢዩ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ አንድ አስገራሚ የሆነ ምዕራፍ እናገኛለን - ምዕራፍ 7፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ነቢዩ ዳንኤል ከአላህ ትንቢታዊ ራእይ ተቀበል፡፡ ራእዩ ወደፊት ስለሚሆኑ ክስተቶች ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን በማመልከት በአላህ ሉአላዊነት ላይ ያተኩራል፡፡

ምዕራፉ የሚጀምረው ነቢዩ ዳንኤል አራት ኃይለኛ አውሬዎች ከባህር ሲወጡ በሚያየው ራእይ ነበር፡፡ ነቢዩ ዳንኤል “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባህር ሲያናውጡ ሌሊት በራእይ አየሁ፤ እርስ በርሳቸውም የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ” ይላል (ዳንኤል 7፡2-3)፡፡ ይህ ራእይ በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ውስጥ ከተጠቀሰው ከንጉሡ ናቡከድናፆር ሕልም ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በዚህ ራእይ ውስጥ የታዩት አራቱ አራዊት አራት ተከታትለው የሚነሱ የምድር መንግስታትን ይወክላሉ፡፡ እነርሱም፡- ባቢሎን፣ ሜዶና ፋርስ፣ ግሪክ፣ እና ሮም ናቸው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል በቁጥር 17 ውስጥ እንዳብራራው “አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሱ መንግስታት ናቸው፡፡” ይህ መረዳት ከታሪክ መረጃዎች ጋር የሚስማማ ሲሆን በምዕራፍ 2 ውስጥ ከሚገኘው ትንቢታዊ መዋቅር ጋር የሚስማማ ነው፡፡

እስቲ እያንዳንዱን አውሬና ያለውን ቦታ እንገምግም፡-

  1. 1. ሁለት ክንፎች ያሉት አንበሳ

- ዳንኤል 7፡4 - ባቢሎን ከ605 እስከ 539 ም.ዓ.

የመጀመሪያው አውሬ የባቢሎንን መንግስት የሚወክል ሲሆን ናቡከድናፆር ገናና ገዢዋ ነበር፡፡ በነቢዩ ዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ውስጥ ንጉሡ በሕልም ካየው ሐውልት ባቢሎን በወርቁ ራስ ትመሰላለች፡፡ ባቢሎን በባለጠግነቷ ትታወቅ ነበር፡፡ የአውሬዎች ሁሉ ንጉሥ የሆነው አንበሳው የሚወክለው የባቢሎንን መንግስት ነው፡፡ የንስር ክንፉ ደግሞ በፍጥነት አለምን መቆጣጠሩን ያመላክታል፡፡ ይሁን እንጂ ክንፎቹ እንደሚነቃቀሉ ትንቢቱ አመላክቷል፡፡ ይህም የባቢሎን ስልጣን አንድ ቀን እንደሚያበቃ ያሳያል፡፡

  • 2. ሦስት የጎድን አጥንቶችን በአፉ የያዘ ድብ -

ዳንኤል 7፡5 - ሜዶና ፋርስ

ሁለተኛው አውሬ በሜዶናዉያንና በፋርሶች ጥምረት የተቋቋመ የሜዶና ፋርስ መንግስትን ይወክላል፡፡ ይህ መንግስት ባቢሎንን አሸንፎ ስልጣን ያዘ፡፡ በነቢዩ ዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ውስጥ በሐውልቱ የብር ደረትና እጆች ይመሰላል፡፡ ጥቅሱ እንደሚገልጸው ይህች አውሬ ስጋን የምትዘነጣጥል ነች፡፡ ይሄም የመንግስቱን ጭካኔ ያሳያል፡፡ በአፉ ውስጥ የነበሩ ሦስቱ የጎድን አጥንቶች በከባድ ጭካኔና ኃይለኝነት የተሸነፉ የሊቢያን፣ የግብጽንና የባቢሎንን የወሰን ክልሎችን ይወክላሉ፡፡

  • 3. አራት ክንፎችና አራት ራሶች ያሉት ነብር የሚመስል አውሬ

ዳንኤል 7፡6 (ግሪክ - 331 እስከ 168 ም. ዓ.)

ሦስተኛው አውሬ በታላቁ እስክንድር የተመራውን የግሪክ መንግስት የሚወክል ነው፡፡ ይህ ነብር አራት ክንፎች ነበሩት፡፡ ይህም የግሪክን አስገራሚና ፈጣን ድል የሚያሳይ ነበር፡፡ “ታላቁ” የሚል ስያሜ የተሰጠው እስክንድር ሰፊ ቦታን የተቆጣጠረ ታላቅ የጦር ስልት ቀያሽ ነበር፡፡ በነቢዩ ዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ውስጥ ግሪክ የተወከለችው ከነሐስ በተሰራው የሐውልቱ ወገብና ጭኖቹ ነው፡፡ እስክንድር ገና በለጋ ዕድሜው ሲሞት አራቱ የጦር መኮንኖቹ መንግስቱን ተከፋፈሉት፡፡ ይህም በነብሩ አራት ራሶች የሚመሰል ነው፡፡

  • 4. የብረት ጥርሶች የነበሩት የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ አውሬ

- ዳንኤል 7፡7 - (ሮም - 168 ም.ዓ. እስከ 476 ዓ. ም.)

አስፈሪና አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ አራተኛው አውሬ ነቢዩን ዳንኤልን በጣም አስደነቀው፡፡ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ይህም ያገኘውን ሊዘነጣጥልና ሊያጠፋ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ አስርቱ ራሶች ይህ መንግስት ሐይል ማሰባሰቡን የሚወክል ነው፡፡ በነቢዩ ዳንኤል ምዕራፍ 2 ውስጥ የሮም መንግስት የምትወከለው በሐውልቱ የብረት እግሮች ነው፡፡ ሮም ዓለምን የገዛችባቸው ዘመናት በግጭትና ጭካኔ የታወቀ ነበር፡፡ አስርቱ ራሶች በመጨረሻ የሮም መንግስት ለአስር ግዛቶች እንደምትከፋፈል የሚያሳይ ነበር፡፡ ይሄም የዛሬውን አውሮፓ ፈጠረ፡፡

በተጨማሪም፣ ነቢዩ ዳንኤል ከአስርቱ ቀንዶች መካከል በቅሎ ሦስቱን ቀንዶች የሚነቃቅል ሌላ ቀንድ ተመለከተ፡፡ ይህ ትንሽ ቀንድ ታላቅ እንደሚሆን፣ የሰው ዓይኖች የሚመስሉ ዓይኖችና ስድብና ትዕቢት የሚናገርበት አፍ እንደነበረው ይናገራል (ዳንኤል 7፡8-11)፡፡ ቀንዱ የሮምን ሐይማኖታዊ ገጽታ የሚወክል ነው፡፡ ይህ የሐይማኖት ሐይል በእግዚአብሔር ቦታ ራሱን እንደሚያስቀምጥ፣ ዘመንና ሕግን እንደሚሽር፣ እና ታማኞችን እንደሚያሳድድ ምዕራፉ ያመላክታል፡፡

ራእዩ ሲቀጥል ነቢዩ ዳንኤል በዘመናት የሸመገለው (ጥንታዌ ጥንቱ) የእሳት ነበልባል በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥና ፍርድ ሲጀምር ተመለከተ (ቁ. 9-10)፡፡ ይህ አላህን፣ ሉአላዊነቱንና ዘላለማዊነቱን የሚገልጽ ራእይ ነው፡፡ ይህ ራእይ አላህ በሕዝቦችና በግለሰቦች ዕድል ላይ የሚወስንበትን ሰማያዊውን ፍርድ የሚወክል ነው፡፡

በተጨማሪም ነቢዩ ዳንኤል የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ወደ ጥንታዌ ጥንቱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ “በሌሊት ባየሁት ራእይ የሰውን ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ” ይላል (ቁ.13)፡፡ ይህ የሰውን ልጅ የሚመስለው ስልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል የተሰጠው ኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ነው (ቁ. 14)፡፡ ይህ ትእይንት የኢሳን ወደ ምድር ዳግም መምጣትና በአለም መንግስታት ላይ የሚሰለጥነውንና ክፋትን የሚደመስሰውን የዘለዓለማዊ መንግስቱን መቋቋም የሚያመለክት ነው፡፡

የራእዩ ትርጓሜ በመልዓኩ ጅብሪል በኩል ለነቢዩ ዳንኤል ተሰጠው፡፡ መንግስታት ተከታትለው ቢነሱና ትንሽዋ ቀንድ ከሮም መንግስት መካከል በቅላ የአላህን (ሱ.ወ.አ) ሕዝብ አሳድዳ ዘመናትንና (በዓላትንና) ሕግን ለመለወጥ ብትሞክርም የፍርድ ችሎቱ መሰየሙ አይቀርም፣ ቅዱሳንም መንግስትን ይወስዳሉ (ቁ. 22)፡፡

ይህ ትንቢታዊ ራእይ ትልቅ ጠቀሜታ ያለውና በዓለም ታሪክ ሁሉ የአላህን ታማኝነትና ሉዓላዊነት የሚያሳይ ነው፡፡ ምንም ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም የማታ ማታ የአላህ ድል የተረጋገጠ መሆኑንና የዘለዓለም መንግስቱም በኢሳ አል-መሲህ (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ገዥነት ሥር እንደሚቋቋም ለሙኢሚኖች ተስፋን የሚሰጥ ነው፡፡

More Stories
When Is a Dream from Allah?
አማርኛ