ነቢዩ ኢብራሂም ሃገሩን ለቆ ወደ ግብጽ ከወረደ በኃላ በጌራር ምድር ኖረ፡፡ ሚስቱ ሣራ በጣም ቆንጆ ሴት ነበረች፡፡ ኢብራሂምም ከሣራ ውበት የተነሳ ለህይወቱ ፈራ ምክንያቱም የምድሪቱ ሰዎች ፈጣሪ አላህን አይፈሩም ነበር፡፡ ስለዚህ ሣራ እህቴ ነች ብሎ ለመናገር ወሰነ፡፡
የጌራር ንጉሥ አቢሜሌክ ሣራ ሚስቱ ትሆን ዘንድ ወደ ቤተመንግስት አስጠራት፡፡ “ኢብራሂም ከዚያ ተነስቶ ወደ ኔጌብ አካባቢ ሄዶ በቃዴስና በሱር መካከል ሰፈረ፤ ለጥቂት ጊዜም በጌራራ ተቀመጠ፡፡ በዚህም ኢብራሂም ሚስቱን ሣራን ‘እህቴ ናት’ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ መልእክተኛ ልኮ ሣራን ወሰዳት” (ተውራት ዘፍጥረት 20፡1-2)፡፡
ነቢዩ ኢብራሂም የአላህ ነቢይ ቢሆንም በዚህ ወቅት እንደ ሰው ድካሙ ታየ፡፡ ሣራ እህቴ ነች በማለቱ የአላህን ፍጹም ጥንቃቄ ተጠራጠረ፡፡ የአባቱ ልጅ ስለነበረች ሣራን እህቴ ነች ብል በአላህ ዘንድ ውሸታም አያሰኘንም ብሎ አሰበ፡፡ ነገር ግን የእናቱ ልጅ አልነበረችም፤ ይህም በታውራትና በሐዲዝ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ግንኙነታቸውን መደበቅ ትክክል አልነበረም፡፡ ከሐቀኝነት ያፈነገጠ ምንም ነገር በአላህ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡
አላህ ስለ ሣራ እውነተኛውን ነገር በሕልም ለንጉሥ አቢሜሌክ ገለጠለት፡፡ “አላህም በአንድ ሌሊት በህልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ ‘እነሆ በወሰድካት ሴት ምክንያት ምውት ነህ፤ እርሷ ባለ ባል ናት’ አለው፡፡ አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ ‘ጌታ ሆይ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን?’ ደግሞስ ራሷም ብትሆን ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረኩት በቅን ልቦናና በንጹህ እጅ ነው፡፡ አላህም በህልሙ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢያት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው፡፡ አሁንም ሚስቱን ለሰውዬው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ’” (ታውራት ዘፍጥረት 20፡3-7)፡፡
የአላህ ዕቅድ ፍጹም ነው፡፡ እርሱ ታማኝና እውነተኛ ነው፡፡ በማግሥቱም አቢሜሌክ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ነገራቸው፤ ሣራም ወደ ባሏ እንድትመለስ ኢብራሂምን አስጠራው፡፡ “ከዚያም አቢሜሌክ ኢብራሂምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣህብን? ከዚያም አቢሜሌክ ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል ኢብራሂምን ጠየቀው (ታውራት ዘፍጥረት 20፡9-10)፡፡
“ከዚያም አቢሜሌክ በጎችና የቀንድ ከብቶች ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለኢብራሂም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት፡፡ አቢሜሌክም ኢብራሂምን ‘እነሆ፣ አገሬ አገርህ ናት፤ በፈቀድክበት ሥፍራ መኖር ትችላለህ’ አለው፡፡ ሣራንም ‘እነሆ ለወንድምሽ ለኢብራሂም 1000 ጥሬ ብር እሰጠዋለሁ፤ ይህም በአንቺ ላይ ለተፈጸመው በደል ካሣ እንዲሆንና አብረውሽ ያሉ ሁሉ እንዲያውቁት ነው፤ በዚህም ንጽሕናሽ ይረጋገጣል’ አላት፡፡ ከዚያም ኢብራሂም ወደ አላህ ጸለየ፤ አላህም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት አገልጋዮቹን ፈውሳቸው፤ እንደ ገናም ልጅ ለመውለድ በቁ፡፡ አላህ በኢብራሂም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት የሚገኙትን ሴቶች ማሕፀናቸውን ሁሉ ዘግቶ ነበርና” (ተውራት ዘፍጥረት 20፡14-18)፡፡
አላህ እንደገና እውነትን በሕልም እንደሚገልጥ አረጋግጦ ነቢይ ቢሳሳት እንኳን ዕቅዶቹና ሃሳቡ እንደማይሰናከል አሳየ፡፡ በዚህ ባልተለመደ አኳሃን ንጉስ አቢሜሌክ የአላህን ታላቅነትና ምህረቱን ተገነዘበ፡፡ በተጨማሪም ንጉሡ ትልቅ ስህተት እንዳይሳሳት ከለከለው፤ ምክንያቱም እውነቱን አላወቀም ነበርና፡፡ ኢብራሂምም የሆነውን ለማብራራትና በንጉሡ ቤተሰብ ላይ ታዉጆ የነበረው እርግማን እንዲከለከል ለመማለድ እድል አገኘ፡፡ እንደዚሁም አላህ ሣራን ጠበቃት፣ ለነቢዩ ኢብራሂም ደግሞ የሚያስፈልገውን በረከት ሰጠው፡፡