ነቢዩ ዳንኤል ከአላህ ነቢያት መካከል አንዱ ነው፡፡ በቁርዓን ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ነገር ግን በሐዲዞችና በእስልምና ትውፊቶች ውስጥ ስለእሱ ማንበብ እንችላለን፡፡ ሙሉ ታሪኩን በታውራት ውስጥ እናገኛለን፡፡
ሕልሞች አላህ እቅዶቹንና ትንቢቶቹን የሚገልጽባቸው ዘዴዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አተረጓጎማቸው ጥናትና ጸሎት ይጠይቃል፡፡ ነቢዩ ዳንኤል የዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ሕዝቡን ስለሚገጥማቸው ነገር፣ ወደፊት ስለሚነሱ መንግስታቶች፣ እንደዚሁም ስለሚመጣው የፍርድ ቀን ከአላህ ራዕይን ተቀብሏል፣ ሕልሞችንም ተርጉሟል፡፡
አንድ ሌሊት የባቢሎን መንግስት ንጉሥ የነበረው ናቡከድናፆር እንቅልፍ የነሳውና በኋላም ከአህምሮው የጠፋ ሕልም አየ፡፡ “ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም ዐለመ፤ መንፈሱ ታወከ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ” (ዳንኤል 2፡1)። ነገር ግን አስፈላጊ መልዕክት እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ስለዚህ የቤተመንግስቱ ጠቢባንና አማካሪዎች ሕልሙንና ትርጉሙን እንዲገልጡለት ጠየቀ፡፡ “ያለመውንም ሕልም እንዲነግሩት ንጉሡ ጠንቋዮችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በፊቱ ቆሙ፤ እርሱም፣ “አንድ ሕልም ዐለምሁ፤ ሕልሙም ምን እንደ ሆነ ለማወቅ መንፈሴ ተጨንቋል” አላቸው። ከዚያም ኮከብ ቈጣሪዎቹ ለንጉሡ በአረማይክ ቋንቋ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልምህን ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም እንፈታልሃለን” አሉት” (ዳንኤል 2፡2-3)፡፡ ይሁን እንጂ ማናቸውም የንጉሡን ሕልም መግለጥ አልቻሉም፡፡ ንጉሡ በጣም ተበሳጭቶ በባቢሎን ቤተ መንግስት ያገለግሉ የነበሩትን ጠቢባን በሙሉ ለመግደል ወሰነ፡፡ ከእነርሱ መካከል ወደ ባቢሎን በምርኮ የተወሰደውና አላህን በታማኝነት የሚያገለግለው ወጣቱ ዳንኤል ነበረ፡፡ የተፈጠረውን ነገር ከተረዳ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርቦ የንጉሡን ችግር ለመፍታትና የሞት አዋጅ የታወጀባቸውንም ነጻ ለማውጣት ጊዜ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ “በዚህን ጊዜ፣ ዳንኤልም ገብቶ ሕልሙን ይተረጕምለት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው” (ዳንኤል 2፡16)።
ዳንኤል የአላህን ራሃመት (ምህረት) እና ጥበብ ለማግኘት በጸሎት በአላህ ፊት ቀረበ፡፡ ከዚያም አንድ ሌሊት ሕልሙ ተገለጠለት፡፡ “ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ” (ዳንኤል 2፡19)፡፡ ሕልም በእርሱና በቃሉ ብቻ ሊተረጎም እንደሚችል ስለገባው ክብርን ሁሉ ለአላህ ሰጠው፡፡ ከዚያም ዳንኤል በንጉሥ ናቡከድናፆር ፊት ቀርቦ በድፍረት የሕልሙን ምስጢር ገለጠለት፡- “ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ” (ዳንኤል 2፤31)፡፡ ዳንኤል ሕልሙን መግለጥ ሲጀምር ናቡከድናፆር ረስቶት የነበረውን ሕልሙን ወዲያዉኑ አስታወሰው፡፡ ዳንኤል በሕልም የታየውን ምስል መግለጽ ቀጠለ፡ - “የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤ ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ። ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጕሙን ለንጉሥ እንናገራለን” (ዳንኤል 2፡32-36)።
ሕልሙን ከነገረው በኋላ ትርጉሙንም ለንጉሡ ነገረው፡- “ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤ የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል። በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቅቃቸዋል። እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደ ሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል። ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም። በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው” (ዳንኤል 2፡37-45)፡፡
በዚህ ማብራርያ ውስጥ አላህ የገለጠውን ዳንኤል ለንጉሡ እንደገለጠለት እናያለን፡፡ መንግስቱ እንደሚያልፍና፣ ከእርሱ መንግስት የሚያንስ ሌላ መንግስት እንደሚነሳ፤ እንደዚሁም ሌሎች በምስሉ የተለያዩ ክፍሎች የተወከሉ መንግስታት ተከታትለው እንደሚነሱ ገለጠለት፡፡ ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ናቡከድናፆር ሕልሙን ካየ ከስድሳ አመት በኋላ ባቢሎን በሜዶ ፋርስ መንግስት (539-331 ም.ዓ.) እጅ ወደቀች፡፡ ከሜዶና ፋርስ መንግስት ቀጥሎ ደግሞ የግሪክ መንግስት ተነሳ (ከ331-168 ም.ዓ.)፡፡ ከዚያም የሮም መንግስት (168 ም.ዓ. እሰከ 476 ዓ.ም.)፤ በኋላም የሮም መንግስት ወደ ሌሎች ብዙ ግዛቶች ተከፋፈለች (የአውሮፓ መንግስታትን የሚወክሉ የሸክላና የብረት ቅይጥ)፡፡
እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ መጥቶ የምስሉን እግሮች የመታው ድንጋይ የኢሳ አል-መሲህን (ሠላሙ በእኛ ላይ ይሁን) ዳግም ምጽአትና ዘለዓለማዊው የሠላምና የአንድነት መንግሥቱ መቋቋሙን ያመላክታል፡፡ ታሪካዊ እውነታዎች ዳንኤል ለንጉሥ ናቡከድናፆር የገለጠው ራዕይ እውነተኛ እንደነበረ ያሳያሉ፡፡ ይህ ደግሞ የአላህ ዕቅድ የማይቀር መሆኑንና የመጨረሻው የትንቢቱም ክፍል፣ ማለትም የኢሳ አል-መሲህ ዳግም ምጽአትም እንደሚፈጸም ተስፋ ይሰጠናል፡፡
ከዚህ ሕልም ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንማራለን፡-
- 1. አላህን እንጂ ጣዖታትን ማምለክ እንደሌለብን
- 2. የሕልምን እውነተኛ ትርጉም የሚገልጠው አላህ መሆኑንና እርሱም ሰዎችን እንደሚጠቀም
- 3. አላህ የዓለምን ታሪክ እንደሚቆጣጠር
- 4. አላህ በሕልም እንደሚናገረን፡፡