ያደኩት በአሜሪካ አገር ሙስሊሞች/አረቦች በሚበዙበት አካባቢ ነው፡፡ አስተዳደጌ በጣም ኃይማኖተኝነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚንጸባረቅበት ሁኔታ ውስጥ ነው ብዬ መግለጽ አልችልም፡፡ ነገር ግን የኢስልምና ስርዓቶች በቤታችን ውስጥ ጠንክረው ይንጸባረቃሉ፡፡ ያለማወላዳትም እንድንከተላቸው ይጠበቃል፡፡ በልጅነቴ ረመዳንን በየዓመቱ በጉጉት ስጠባበቀው ትዝ ይለኛል፡፡ ለረመዳን አስቤዛ ለመግዛት ወደ ሱቅ ከወላጆቼ ጋር ስሄድና ወላጆቼ የሚገዙት አስቤዛ ተቆልሎ ሳይ ለዓመቱ ሙሉ የሚበቃን ይመስለኝ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡ በጣም የምወደውን የኮክ ማርማላታ መግዛት አለመግዛታቸውን ሁሌ እከታተል ነበር፤ እነርሱም ይገዙልኝ ነበር፡፡ ወላጆቼ ሲሰግዱ አይ ነበር፡፡ አባቴ ሁል ጊዜ በእራት ላይ የመጀመሪያውን ጉርሻ ሳይጎርስ ቢስምላሂ አል ራህማን አል ረሂም (በአላህ ስም፤ እጅግ በጣም ሩኅሩህ፣ በጣም አዛኝ በሆነው) ብሎ ሲጀምር ትዝ ይለኛል፡፡ በቤታችን የነበረው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊና ማህበራዊ ግብረገብ ትዝ ይለኛል፡፡ ሕይወት ለኔ ውስብስብ አልነበረም፡፡ ይህ ግን ስለ አላህ መመለስ የማልችላቸው ጥያቄዎች መኖራቸውን እስከማስተውል ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ እርሱ በእውነት ማንነው? ሰማዩ ላይ እየተንሳፈፈ ወደታች ይመለከተናል? በኃጢያተኞች ላይ በፍርድ ቀን ያደርጋል ሲባል የሰማሁትን በእውነት ያደርጋል? ለምንድነው ወደ እርሱ የመቅረብ ስሜት የማይሰማኝ? ወደ እርሱ ስጸልይ ለምንድነው ምንም ነገር የማይሰማኝ? እንዴት ነው የሱስ ሳይሰቀል ሊቀር የሚችለው?
አንድ ቀን ማንነቴ ሁሉ የተገነባበትን እምነቴን ጥያቄ ውስጥ እንደማስገባ አላወቅሁም ነበር፡፡ በማውቃቸው ነገሮች ላይ ጥያቄ ለማስነሳት ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን አላህ አስቀድሞ ፈለገኝ፡፡ አንድ ቀን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጓደኛዬ (አሁን የሕይወት አጋሬ) ጋር ተቀምጠን እንደነበርን ትዝ ይለኛል፡፡ በጣም ክፉ ነገር ያደረገውን ሰው ለምን ይቅር እንዳለው ጠየቅሁት፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ የሚጠብቀው እንደሆነና ሌላ አማራጭ እንዳልነበረው ነገረኝ፡፡ ይህን ሰው በፍጹም ልረዳው አልቻልኩም፡፡ ይቅርታውን እንደ ድክመት ነበር የወሰድኩት፡፡ ለረጅም ጊዜ ስከታተለው አንድ ልዩ ነገር እንዳለሁ አስተዋልኩ፤ ምን እንደሆነም ማወቅ ፈለክሁ፡፡ የአላህ መንፈስ ከእርሱ ጋር እንደነበረ እኔ አላወቅሁም ነበር፡፡ ያ መንፈስ ከዚህ በፊት አይቼ የማላውቀውን ነገር አሳየኝ፤ የአላህንም ማንነት በትንሹ ገለጠልኝ፡፡ ሳንቋሽሸው ያደኩት ደግነትና ምህረት ተገለጠልኝ፡፡ በተጨማሪም ገሸሽ ላደርገው የማልችል መንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ እንዳለሁም አላውቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ለዘመናት ለማወቅ ጉጉት የነበረኝን ስለክርስትና እና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የያኔ ጓደኛዬን ለመጠየቅ ተገደድኩ፡፡ ጥያቄዎቼን ሳያጣጥል እንደሚመልስልኝ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ነበር የጠየቅሁት፡፡ የመጀመሪያ ጥያቄዬ፤ “እንዴት ነው አላህ ልጅ አለው የምትሉት? እርሱ አይወልድም፣ ከምንም ሆነ ከማንም አይወለድም” የሚል ነበር፡፡ አጥጋቢ መልስ ነበር ያገኘሁት፡፡ “ልጅ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ በስተመጨረሻ ተረዳሁ፡፡ “እንዴት ነው በተበረዘና በብዙ ሰዎች በተጻፈ መጽሐፍ የምታምኑት? ቁርዓን እኮ ከጅምር ጀምሮ ምንም ለውጥ አልተደረገበትም፤ ታውራትም እንደዚሁ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የምትሉት ነገር ግን ሰው ሰራሽ ነገር ነው፡፡” እርሱም ጥያቄዎቼን መለሰልኝ፤ ታውራትም የመጽሐፍ ቅዱስ አካል መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ብሉይና አዲስ ኪዳን ምን እንደሆኑም ተረዳሁ፡፡ የሙት ባህር ጥቅሎችን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት የሚያረጋግጡ በሺሆች የሚቆጠሩ ቀደምት ጽሑፎች እንዳሉም አወቅሁ፡፡ ከዚያም ከኢስልምና አስተምሮዎች መካከል በአንዱ እንደማላምን ነገርኩት፤ እርሱም ዒሳ አልተሰቀለም የሚለው ነው፡፡ ይህን በፍጹም ተቀብዬው አላውቅም ነበር፤ ምክንያቱም በእምነቶች መካከል ለሚታዩት ክፍፍሎች ሁሉ አላህን ተጠያቂ የሚያደርግ ይመስላል፡፡ አላህ ሰዎችን ግራ ያጋባል የሚለው አያሳምንም፡፡
ከብዙ ውይይትና ስለ አላህ እና ስለ ዒሳ ብዙ ካወቅሁ በኃላ እነዚህን ጉዳዮች መርሳት አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ልቤ ግን የሚለኝ ሌላ ነበር፡፡ ኢስልምናን መገዳደር ከመፍራቴ የተነሳ ይሄን የተማርኩትን አዲስ መረጃ ለብዙ ሳምንታት ችላ ለማለት ሞከርኩ፡፡ ትልቁ ኃጢያት ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ ይሄኔ ነበር ሕልሞቼ የጀመሩት፡፡ ዒሳን በሕልሜ ማየት ጀመርኩ፤ ስለሚመጣው ነገር አቅጣጫ ሲያሳየኝ፣ እርሱን ከማወቅ ጋር ሊመጡ ያሉ ደስታዎችና ሐዘኖችን አሳየኝ፡፡ በሕይወቴ ውስጥ የሆነ ነገር እየሆነ እንደነበረ መካድ አልቻልኩም፡፡ የሚያስፈራ ቢሆንም በዚያው ልክ ደግሞ በደስታና በሰላም የሚሞላ ነበር፡፡ ስለ አላህና ስለ ዒሳ ለማወቅ የበለጠ እንደምጥርና እንደማጠና ወሰንኩ፡፡ ወደ እርሱ መጸለይ እንደማይሠራ ለማሳየት አንድ ቀን ምሽት ወደ ዒሳ ጸለይኩኝ፡፡ ከጸሎቱ በኋላ የሆነው ነገር ተዓምር ነበር፡፡ ደጋግሜ ጸለይኩኝ፡፡ በዓይኖቼ ፊት ተዓምራቶች መፈጸም ጀመሩ፡፡ በመጨረሻ ዕድሜዬን ሁሉ የተጠማሁትን ከአላህ ጋር ግንኙነት እንዳለኝ ተሰማኝ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዒሳ ከነቢይነት የዘለለ ማንነት እንዳለው የበለጠ እየተረዳሁ ሄድኩኝ፡፡ በመጨረሻም ዒሳ በእርግጥም አምላክ መሆኑን ተገነዘብሁ፡፡ ከአላህ ጋር አንድ እንደሆነና የአላህም መንፈስ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ልክ እርሱን እንዳወቅሁኝ ሕይወቴ ተስተካከለ፡፡ ግድድሮሾችና መስዋዕቶች የበዙበት ነው፤ አንዳንዶቹን ዛሬም ቢሆን እጋፈጣቸዋለሁ፡፡ ቀላል ጉዞ አልነበረም፡፡ ከእምነቴ ጋር ተቆራኝቶ ያለው ባህሌ በአብዛኛው ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡ ምን ማድረግ እንደምችል አላውቅም ነበር፡፡ በሆነ መልኩ አሁንም መልሱን ለማግኘት እጥራለሁ፡፡ ነገር ግን የሱስ ከእኔ ጋር እንደሆነ፣ እንደሚወደኝና ወደ እርሱ የምመጣበትን ቀን አይቶ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ በማላየው ጊዜም ከጎኔ አይለይም፡፡ በእርሱ መስዋዕትነት ነው ከዚህ ሕይወት ባሻገር ያለውን ዕድል ያገኘሁት፡፡ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? ይሄን ፍቅር አሁንም ልረዳ እየሞከርኩ ነው፡፡ ለመራኝ የእምነት ጉዞና ዒሳ አል-መሲህ በሕይወቴ ማን እንደሆነ፣ እርሱን እንዳውቅና እንድረዳው ስለረዳኝ አላህን አመሰግናለሁ፡፡ ጸሎቴ ሙስሊሞች ሁሉ ይህን ጉዞ እንዲለማመዱና አላህ ለእያንዳንዳችን ያለውን የፍቅሩን ባለጠግነት እንዲቀምሱት ነው፡፡