ቁርአን እንዲህ ይላል፡- “ለነሱ በቅርቢቱ ሕይወትም በመጨረሻይቱም ብስራት አላቸው፤ የአላህ ቃላት መልለወጥ የላትም፤ ይህ እርሱ ታላቅ እድል ነው” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡64)፡፡
ብዙ ፈሳሪዎች (የቁርዓን ተንታኞች) በዚህ አለም ላይ ያለው (በቅርቢቱ) ብስራት ሕልሞችና ራዕዮች ናቸው ብለዋል፡፡ ለምሳሌ፤ ኢብን ካቲር በተፍሲሩ ውስጥ “ለነሱ በቅርቢቱ ሕይወትም በመጨረሻይቱም ብስራት አላቸው” በሚለው ላይ “መልካም ራዕይ በሕልም ለሙኢሚን ይታያል ወይም ይሰጠዋል” (ተፍሲር ኢብን ካቲር)፡፡
ስለ ሕልም አፈታት በሚያወሳው መጽሐፉ ውስጥ ኢብን ኩታይባ አል-ዲናዋሪ እንዲህ ይላል፡- “ሰዎች በተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮች ከሚመራመሯቸው ነገሮች ውስጥ እንደ ሕልም ድብቅ፣ ውስብስብ፣ ከፍ ያለ፣ ክቡር፣ ከባድና አስቸጋሪና ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሕልሞች የመገለጥና የነቢይነት አካል ናቸው፡፡”
አናስ ኢብን ማሊክ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል ብለው ተናግረዋል፡- “የጻድቅ ሰው መልካም ሕልም (የሚፈጸም) ከአርባ ስድስት የነቢይነት ክፍሎች አንዱ ነው” (ሰሂህ ቡኻሪ)፡፡
ሦስት ዓይነት ሕልሞች አሉ፡- ኢማም አል-ትርሚዲ አቡ ሁሬይራ መናገራቸውን ከሙሃመድ ኢብን ሲሪን እንደሰሙት፣ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- “ሦስት ዓይነት ሕልሞች አሉ፡-1) ሕውነተኛ ሕልም፤ 2) ሰው ለራሱ የሚናገረው ሕልም (ማለትም በቀን ስታስበው የዋልከውን ሌሊት በህልም ታያለህ)፤ 3) ከሰይጣን የሚላክ ሕልም (ሸይታኒ) - እርሱ በህልሙ ውስጥ ሆኖ ሊያሳዝናችሁ የሚያደርገው ማለት ነው፡፡”
ከአላህ የሚላኩ ሕልሞች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ኢብን ባታል እንዲህ ብለዋል፡- “ሕልሞች ሁለት ዓይነት ኛቸው፡- ግልጽ የሆነ ሕልም - ለምሳሌ አንድ ሰው በህልሙ ለሚያዉቀው ሰው ቴምር ቢሰጥ በቀን ለዚያው ሰው ቴምሩን ቢሰጥ እንደ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሕልም ምንም ትርጉም አይፈልግም፡፡ ሁለተኛው በምልከት የሚገለጥ ሕልም ሲሆን ሕልም የመፍታት እውቀትና ልምድ ያለው ሰው ካልተረጎመልህ በስተቀር መረዳት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹ ጥንቃቄ የሚፈልጉና ውስብስብ ናቸው፡፡”
መልካም ሕልሞችን ለሌሎች ሰዎች መንገርን በተመለከተ ሃዲዝ ውስጥ ግልጽ አቅጣጫዎችን እናገኛለን፡፡ ነገር ግን መጥፎ ሕልሞች ለሰዎች መነገር የለባቸውም፡፡ አቡ ሰይድ አል-ኩሁድሪ እንዲህ አሉ፡- ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- “ከእናንተ መካከል ማንም ደስ የሚያሰኘው ሕልም ካየ ሕልሙ ከአላህ ነው ማለት ነው፤ ስለዚህ አላህን ማመስገን አለበት፣ ለሌሎችም ማውሳት አለበት፡፡ ነገር ግን ሌላ ነገር ካየ - ማለትም የማያስደስተው ሕልም - እሱ ከሰይጣን የተላከ ሕልም ነው፡፡ ከክፉው ለማምለጥ ከአላህ ከለላ መጠየቅ አለበት፤ ስለማይጎዳው ለማንም መንገር የለበትም፡፡” (ሰሂህ ሙስሊም)፡፡
በመጨረሻው ዘመን እውነተኞ ሕልሞች ይበረክታሉኢብን ሲሪን እንዲህ አሉ፡- “አቡ ሁሬይራ እንዲህ ሲሉ ሰማሁ፡- ነቢዩ ‘ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ የሙኢሚኑ ሕልም በአብዛኛው አይዋሽም’” (ሰሂህ አል-ቡኻሪ)፡፡
ኢብን አቢ ጃመራሀ “ሙኢሚን በመጨረሻው ዘመን እውነተኛ ሕልም የሚያይበት ምክንያት፣ በሐዲዝ ውስጥ እንደተገለጸው ሙኢሚን እንደ መጻተኛ ይሆናል - ኢስላም እንደ መጻተኛ መስሎ ነው የተጀመረው፤ ስለዚህ ወደ መጀመሪያው ሁኔታው ወደ ምጻተኝነት ይመለሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ (ሕልም) ለመጻተኞቹ የምስራች ያበስራል” (ሰሂህ ቡኻሪ)፡፡
አቤድ አላህ ኢብን ኡመር እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፡- በመጨረሻ ሰባቱ የረመዳን ቀናት ውስጥ በኃይል ምሽት (በሌይለት አል-ቃድር) ለአንዳንድ ሰዎች ሕልም ታይቷቸው ነበር፡፡ ነቢዩም እንዲህ አሉ፡- “ሕልሞቻችሁ እርስ በርስ ይደጋገፋሉ፤ ስለዚህ የቀድር ሌት በረመዳን ሰባቱ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ነች፡፡ ስለዚህ የሚፈልጋት ሰው ሁሉ በመጨረሻዎቹ ሰባት የረመዳን ቀናት ውስጥ ይፈልጋት” (ሰሂህ ቡኻሪ)፡፡
ስለዚህ አላህ ዛሬም በህልምና በራዕይ ይናገራል ምክንያቱም የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ስለሆነ፡፡ ዓለም ሁሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ ነው፡፡
በተውራትም ሆነ በኢንጂል ውስጥ አላህ በቀጥታ ለሰዎች የሚናገር የነበረው በህልምና በራዕይ ነበር፡፡ ተውራትና ኢንጂል አላህ በመጨረሻ ዘመን በህልምና በራዕይ ለሰዎች እንደሚናገር ትንቢት መኖሩን ይናገራሉ፡፡
በተውራት ውስጥ እንዲህ እናነባለን፡- “ከዚህም በኋላ፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤ ጎልማሶቻችሁም ራዕይ ያያሉ” (ተውራት ኢዮኤል 2፡28)፡፡
ኢንጂልም እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገሩሉ፤ ጎልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፡፡ በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ” (ኢንጂል የሐዋርያት ሥራ 2፡17-18)፡፡
ስለዚህ ከአላህ የተቀበሉት ሕልም ካለዎት ለእኛ ከማካፈል አይቆጠቡ፡፡
አላህ ዛሬም በህልምና በራእይ ይናገራል፡፡ የእነዚህን ሕልሞች ትክክለኛ ትርጉም ስንረዳ እንደ ፈቃዱ መኖር እንችላለን፡፡ አሁኑኑ እየተናገረዎት ሊሆን ይችላል፡፡ ምላሽዎት ምንድነው? የህልምዎትን ምንነትና ዓላማ ለመረዳት መጣር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እኛ ደግሞ አላህ የሰጠዎትን ህልም እንዲረዱ ልንደግፍዎት ዝግጁ ነን፡፡