ስሜ ሳሃር ይባላል፡፡ ተወልጄ ያደክሁት በኢራን ነው፡፡ ከተማረና የኢስልምናን ኃይመኖታዊ ስርዓቶች ከሚያከብርና ከሚተገብር ቤተሰብ ነው የተወለድኩት፡፡
አንድ ቀን አባቴ ከሥራ መጥቶ ሳሎን ቁጭ ብሎ እራት ይጠባበቅ ነበር፡፡ እናቴ ስትጠራው አይንቀሳቀስም፡፡ እንዲረዷትና ወደ ሆስፒታል እንዲወስዱላት እናቴ ጎረቤቶቿንና ጓደኞቿን ጠራቻቸው፡፡ የነበረንን ጥሪት ሁሉ ለሕክምናው ጨረስን፤ ነገር ግን ምንም መሻሻል አልነበረም፡፡ ዶክተሮቹ ምን እንደሆነ መናገር አልቻሉም፤ እንዴት እንደሚያክሙትም አላወቁም፡፡ ስለዚህ አባቴ ለብዙ ወራት ቤት ቆየ፡፡
አንድ ቀን እናቴ ውጭ ስትንቀሳቀስ በከተማችን የማይኖር ከአባቴ ጓደኞች አንዱን አገኘችው፡፡ ክርስቲያን ከመሆኑ የተነሳ በደረሰበት ስደት ምክንያት ሰውዬው ወደ ሌላ ሃገር ተሰድዶ ነበር፡፡ እናቴ የአባቴን ሁኔታ ነገረችው፡፡ በዚህ ጊዜ ለ50 ቀናት ሳይንቀሳቀስ አልጋ ላይ ቆይቷል፡፡ ዶክተሮችም ምንም ማድረግ እንዳልቻሉና ትንፋሽ ብቻ እንዳለው ነገረችው፡፡
አባቴን ለረጅም ጊዜ አይቶት የማያውቅ ይህ ሰው አንድ ሐኪም ጓደኛውን ይዞ ቤታችንን መጎብኘት ይችል እንደሆነ በትህትና ጠየቃት፡፡ እናቴ ወደቤታችን እንዲመጡ ጋበዘችው፤ እኛም በጉጉት እንጠብቃቸው ነበር፡፡
በሚቀጥለው ቀን የአባቴ ጓደኛ ወደቤታችን መጣ፡፡ እናቴን፣ ወንድሜንና እኔን ሰላም ካለን በኃላ ቀጥ ብሎ አባቴ ያለምንም እንቅስቃሴ ወደሚተኛበት ክፍል አመራ፡፡ ዶክተር ጓደኛውን አመጣለሁ ብሎ ብቻውን መምጣቱ እናቴን አስገርሟታል፡፡ ነገር ግን ምንም አላለችም፡፡ ወደ አባቴ ጠጋ ብሎ በኃይል እየጸለየ የዶክተሮች ሁሉ ዶክተር እንዲነካውና ጤናውን እንዲመልስለት ጮክ ብሎ ተማጸነ፡፡ የክፍሉ በር ክፍተት ነበረው፡፡ እኔ የ4 ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ በክፉሉ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ሁሉ ቆሜ እመለከት ነበር፡፡
ሰውዬው ከጸለየ በኋላ ደህና ሰንብቱ እያለን ሳለ እኔ ወደ ክፍሉ ውስጥ እያየሁ ስለነበረ አባቴ አልጋው ውስጥ ሲንቀሳቀስ አየሁና ባባ እየተንቀሳቀሰ ነው ብዬ ጮኹኩኝ፡፡ ሁሉም ሰው ወደ አልጋው ሲመለከት ተገረሙና ወደ ክፍሉ ተመለሱ፡፡ አባቴ በአልጋው ውስጥ ጤናማ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ ነቃና አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቀን፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ወደ ጤናማ ሕይወቱ ተመለሰ፡፡ ታሞ እንደነበረ አላስታወሰም፡፡ የቤተሰባችን አባላት በሙሉ ተደነቁ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምንድነው የሆነው? ይህ አምላክ ማን ነው? ይህን አምላክ ዬት እናገኘዋለን?
ያ ሰው ሁሉን ስለፈጠረው አምላክ፣ የዶክተሮች ሁሉ ዶክተር ስለሆነው፣ የጌቶች ጌታና አዳኝ ስለሆነው አል-መሲህ ኢሳ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ይነግረን ጀመረ፡፡
በከተማችን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ፈለግን፣ ነገር ግን በቋንቋችን የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ አጣን፡፡ በአገራችን መጽሐፍ ቅዱስ መያዝ ክልክል ነው፡፡ ስለዚህ፣ የአባቴ ጓደኛ በሊባኖስ ነበር የሚኖረው፤ እርሱ አረብኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠን፡፡ አረብኛ አናውቅም ነበር፤ ስለዚህ አባቴ አረብኛ መማር ጀመረ ምክንያቱም የፈወሰውን የመጽሐፍ ቅዱሱን አምላክ ለማወቅ ስለጓጓ ነበር፡፡ አረብኛን ተምሮ መጽሐፍ ቅዱሱን ማጥናት ጀመረ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠነው በምስጢር ነበር፡፡
ወንድሜ የፍጥረት ታሪኮችን፣ የእስራኤልን ህዝብ ነፃ የመውጣት ታሪክን፣ የየሱስ በመስቀል ላይ የመሞቱ ታሪክን አንብቦ መጽሐፍ ቅዱስ በተስፋ ቃላትና በሰላም የተሞላ መሆኑን ሲረዳ በጣም ተደነቀ፡፡ አዲሱን እምነቱን፣ የተማረውንና ስለመንፈሳዊ ነገሮች ያገኘውን መረዳት ለጓደኞቹ ማካፈል ጀመረ፡፡ ነገር ግን አዲሱን እምነታችንን ለሌሎች ሰዎች ማካፈል አደገኛ ነው ስለተባለ እንደዚህ ማድረግ የለባችሁም ተባልን፡፡ እምነታችንን በምስጢር መያዝ ነበረብን፡፡
አንድ ቀን ፍርሃቱ ጠፋና ከጓደኞቹ ጋር ለመነጋገር ወሰነ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንንና ሌላ አምላክ ማግኘታችንን፣ ይህም አምላክ ሁሉን የፈጠረ መሆኑን፣ ስለ ችግራቸው የሚገደው የፍቅር አምላክ መሆኑን፣ ድንቅ አምላክ፣ መሐሪ አምላክ መሆኑን ነገራቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ጓደኞቹ ለወላጆቻቸው በመናገሯቸው ጉዳዩ ፖሊስ ጋር ደረሰ፡፡
ፖሊስ ወንድሜንና መጽሐፍ ቅዱስን ለመያዝ ወደቤታችን መጡ፡፡ እናቴ ምግብ እያበሰለች ነበር፡፡ ፖሊሶቹ ሲመጡ አይታ መጽሐፍ ቅዱሱን ወስዳ ምድጃ ውስጥ አስቀመጠች፡፡ በዚህ መልኩ ሕይወታችንን ታደገች፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን መሆናችንን የሚያሳይ ማስረጃ ካገኙ ሁላችንም እንገደላለን፡፡
ዕድሜው 16 ዓመት የሆነ ወንድሜ ቤተሰብ ወደማያውቀው ቦታ ተወስዶ ለሶስት ወር ሲያሰቃዩት ቆዩ፡፡ ወደቤቱ ሲመለስ ጥርሶቹ ረግፈው ነበር፤ በእስር ቤት ውስጥ በብዙ የኤሌክትሪክ ንዝረት ስለተመታ የማስታወስ ችሎታውን ሁሉ አጥቶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ጉዳትና መጥፎ ትዝታን ይዞ የተመለሰው ለጓደኞቹ እግዚአብሔር አብንና አዳኙን የሱስን እንደሚያውቅ ስለነገራቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ስደትና ስቃይ የደረሰበት ለእነዚያ ጓደኞቹ እምነቱን ስላካፈላቸው ነበር፡፡
በአገር ውስጥ ምንም እርዳታ ማግኘት አልቻልንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለሕክምና ወደ አውሮፓ እንድንሰደው መከሩን፡፡ ይህንኑን አደረግን፡፡ ከዚያም ከጥቂት ወራት በኋላ የመሞቱን ዜና ሰማን፡፡ ችግሩና ስቃዩ ሁሉ እንዳለ ቢሆንም የሚጠነቀቅልን አባት አለን፡፡
አሁን ክርስቲያን ስለሆን ሌሎች ቤተሰቦቻችን እስልምናን በመካዳችን እንደሚገድሉን ስለዛቱብን ቤተሰባችን ወደ 1300 ኪ.ሜ. ርቆ መኖር ግድ ሆነበት፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስማርና የአሥራዎች እድሜ ክልል ውስጥ እያለሁ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ፡፡ እንድ ጊዜ ስህተት ነው ብዬ የማስበውን ነገር ስለቁርዓን በትምህርት ቤት ጠየቅሁኝ፡፡ ወዲያውኑ ቁርዓን ላይ ጥያቄ ማንሳት ክልክል መሆኑን ነግራኝ አስተማሪዬ አስጠነቀቀችኝ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደገና ስለቁርዓን ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ አስተማሪዬ ወዲያውኑ ፖሊስ ጠርታ እንዲወስዱኝ ጠየቀቻቸው፡፡ አንድ ምስጢራዊ ቦታ ወስደውኝ መስኮት በሌለው ጨለማ ቤት ውስጥ አስቀመጡኝ፡፡ በየቀኑ አንድ ክፉ ሰውዬ ወደ ክፍሉ እየመጣ እንደሚረግመኝ፣ እንደሚሰድበኝና እንደሚያሰቃየኝ ትዝ ይለኛል፡፡ አንድ ቀን ጸጉሬን ላጩኝ፡፡ ጸጉር ለሴት ልጅ ክብሯ ስለሆነና ጸጉር የሌላት ሴት ከሕብረተሰቡ ስለምትገለል ይሄ በአገሪቱ በጣም አሳፋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ ጥፍሬን ነቀሉኝ፡፡ የበለጠ መዋረድና የበለጠ ስቃይ፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔርን ብቻ ተስፋ አደረግሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ውርደትና አካላዊ ህመም መቋቋም እንድችል መጽናናትና እምነትን እንዲሰጠኝ፣ በተባረከው ተስፋም ልቤን እንዲሞላኝ፣ ጠየቅሁት፡፡ እግዚአብሔርን ተስፋ አደረኩኝ፤ እርሱም ሕይወቴን ታደገኝ፡፡ ለአምላኬና ለአዳኜ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ሆኜ ቆምኩኝ፡፡
ሊያስለቅቁኝ ቤተሰቦቼ በጣም ውድ ወረታ ከፈሉ፡፡ ወደ ቤት ስመለስ ፖሊስ ፓስፖርቴን ወስደው ማሕተም አደረጉበት፡፡ ይህ ማለት መማርም ሆነ መስራት አልችልም ማለት ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ያዩት ብቸኛው ምርጫ ከአገር መውጣት ነበር፡፡ ስለዚህ በአውቶቡስ ወደ ሩቅ አገር መጓዝ ግድ ሆነብኝ፡፡ ወዴት እንደምሄድ፣ ማንን እንደማገኝ አላውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን የሚጠነቀቅልኝ የሰማይ አባት እንዳለኝ አውቃለሁ፡፡
በዚያ አገር በጣም ተቸገርኩኝ፤ ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ እርዳታ ጠየቅሁኝ፣ ማንም ሊረዳኝ አልፈለገም፡፡ ከዚያም በዚያ አገር የሚኖር በቴሌቪዥን ላይ የማውቀው ፓስተር ትዝ አለኝ፡፡ ስልክ ቁጥሩ ነበረኝ፡፡ ደውዬ ታሪኬን ነገርኩት፡፡ አንድ ወደ ተለየ አካባቢ እንድሄድ ነገረኝ፡፡ እዚያ ስኖር ሌሎች ምእመናንን አገኘሁ፤ አብረንም መጽሐፍ ቅዱስ እናጠና ነበር፡፡ በዚያ አገርም ጦርነት ተከፈተ፤ ስለዚህ አገሩን መልቀቅ ነበረብኝ፡፡ ነገር ግን ወዴት እንደምሄድ አላውቅም ነበር፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ እንድወጣ እግዚአብሔር በር ከፈተልኝ፡፡ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ በዚያኑ ቀን ተጠመቅሁ፡፡ ያን ቀን በፍጹም አልረሳውም፡፡
አሁን ተማሪ ነኝ፤ የማጠናውም ሥነ-መለኮት ነው፡፡ ጌታዬንና አዳኜን ኢሳ አል-መሲህን እንዲያውቁት መልካሙን ዜና ለሕዝቤ ማካፈል እፈልጋለሁ፡፡ ኢሳ አል-መሲህን ማወቅ ማለት በመከራው መካፈል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ያፈሰሰልኝ ደም እኔ ዛሬ ለእርሱ ከማደርግለት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው ዬትየለሌ ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ኢየሱስ ሲመለስ እኔና ወንድሜ አዲስ አካል ይኖረናል፡፡