አብደላ እባላለሁ፡፡ ፍልስጤማዊ ስሆን አሁን የምኖረው በዮርዳኖስ አገር ነው፡፡ ቤተሰቤ በአማን ከሚገኙ ዋና ዋና ቤተሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ የፍሊስጤምን ጉዳይ በማቀንቀን አባቴ የታወቀ መሪ ነው፡፡ በማህበረተሰባችን ውስጥ ከሚገኙት አክራሪ መሪዎች አንዱ ነው፡፡ አይሁድና ክርስቲያኖች መሬታችንን ወስደው ስደተኛ ስላደረጉን እነርሱን እንድጠላ ተደርጌ ነው ያደግሁት፡፡
አንድ ቀን ፌስቡኬን እያየሁ አንድ ጓደኞዬ ስለ ኢሳ አል-መሲህ ሕልሞች የምጽፍን ሰው በጽሑፍ ሲያጠቃ አየሁ፡፡ ምልልሱን ተከታተልኩ፡፡ ክርስቲያኑ ሰዉዬ በሚለው ነገርና ከቁርዓንና ከሐዲዝ በሚያቀርባቸው መረጃዎች ተገረምኩ፡፡ ተረበሽኩ፤ ልመልስለትም ከጀልኩ፡፡ መልስ ለማግኘት ብዙ ጊዜ በጥናት ማሳለፍ ጀመርኩ፡፡
ከዚያም በአንድ ሕንጻ ውስጥ ሆኜ ሕልም አየሁ፡፡ ሕንጻው ይንቀጠቀጣል፤ ሊወድቅም ነበር፡፡ በድንገት አንድ ነጭ የለበሰና ቡናማ ጸጉር የነበረው ሰው በመስኮት እጁን ዘርግቶ “ከእኔ ጋር ና፤ እኔ እጠነቀቅልሃለሁ” አለኝ፡፡ ሰማዩ በጣም ብሩህ ነበር፡፡ እጆቼን ወደ እርሱ ዘረጋሁ፡፡ በመስኮት ስቦ አወጣኝ፡፡ ከእርሱ ጋር ሆኜ ሙሉ ሰላምና ምቾት ውስጥ የነበርኩ ብሆንም እየወደቅሁ እንዳለ ተሰማኝ፡፡ አረንጓዴ መስክ ላይ አረፍኩኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም፡፡
“ማን ነህ?’ ብዬ ልጠይቀው አሰብኩኝ፡፡ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ የማውቀው መስሎ ታየኝ፡፡ ምንም ማስተዋወቅ አያስፈልገውም የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡ ከእርሱ ጋር ሳለሁ ሰላም፣ ደስታ፣ ተስፋና ፍቅር ተሰማኝ፡፡ ሁሌም ከእርሱ ጋር መቆየት ፈለኩኝ፡፡ መመለስ አልፈለኩም፡፡
በመጨረሻ ድፍረት አገኘሁና ጠየቅሁት፡- “አንተ ማን ነህ?” አልኩት፡፡ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” አለኝ፡፡ ማንነቱን በቀጥታ ተገነዘብሁ፡፡ ኢሳ አል-መሲህ ነው፡፡ ስላንተ የበለጠ ማወቅ እፈልጋለሁ ስለው አንድ መጽሐፍ ሰጠኝ፡፡ ሲመለከተው ኢንጂል ነበር፤ አንብበው አለኝ፡፡
በኢሳ አል-መሲህ አምናለሁ፡፡ የበለጠ ላውቀው አሁን ጉዞ ላይ ነኝ፡፡ በጸሎትዎ ያስቡኝ፡፡ ሕይወቴን ላጣ ስለምችል በዚህ ሥፍራ አዲሱን እምነቴን ለሰው ማካፈል አልችልም፡፡ አይኔን ስለከፈተልኝና የበለጠ እንዳጠናና የበለጠ እንዳውቅ ስላደረገኝ በይነ-መረባችሁ አመሰግናችኋለሁ፡፡