ሩት እባላለሁ፤ ያደግሁትም ጌታዬ የሱስ ክርስቶስ በእግሩ በተመላለሰባት አገር ነው፡፡ ከተማረና የኢስልምና ኃይማኖትን ከሚያከብሩ፣ እንደ ሶላትና ጾም የመሳሰሉ ስርዓቶቹንም ከሚተገብር ቤተሰብ ነው የወጣሁት፡፡ ሶስት አማልክትን ያመልካሉ ብዬ ስላሰብኩ ክርስቲያኖችን እየጠላሁ ነበር ያደኩኝ፡፡ ነገር ግን የሱስ በሕልም ተገልጦልኝ የሕይወቴን ታሪክ ቀየረው፡፡
አምላካችን የተዓምራት አምላክ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ እርግጥ መሆኑን አምናለሁ፤ ምክንያቱም ከእርሱ ጋር የተለማመድኩት የግል ምስክርነቴ ስለሆነ፡፡ አሁን የጌታዬን፣ የአምላኬንና የአዳኜን የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ በመከተል ተጠምቄአለሁ፡፡ ስሜንም ወደ ሩት ቀየርኩት፡፡ በሕይወቴ የምፈልገው ነገር ቢኖር ጌታዬ እንደተመላለሰው መመላለስ ነው፡፡ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” (1ጴጥሮስ 2፡21)። ድምጹን እየሰማን የመንጋው አካል እንድንሆን ነው የጠራን፡፡ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” (ዮሐንስ 10፡27)፡፡
ከመጠመቄ በፊት ስለብዙ ነገሮች እጸልይ ነበር፤ ጥምቀቴም ከጸሎት አርዕስቶቼ አንዱ ነበር፡፡ ከልብ ስጸልይ ነበር፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው” (መክብብ 3፡1)፡፡
በዚህ ወቅት ከአንዳንድ የኃይማኖት ተቋማት ጋር እየተነጋገርኩ ነበር፡፡ ሁሌም በጌታ በኢየሱስ ማደግ ፍላጎቴ ነበር፤ በመጨረሻም አምላኬ ምን ያክል እንደሚወደኝ ገባኝ፤ መዝሙር 119፡105 ላይ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ተብሎ በተጻፈው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን የሕይወቴ ህገመንግስት በማድረግ የእግዚአብሔር ቅሬታ ሕዝብ አካል በመሆን ትዕዛዙንና የኢየሱስን እምነት ለመጠበቅ ወሰንኩኝ፡፡ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው” (ራዕይ 14፡12)። “የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” ተብሎ እንደተጻፈ የሰዎችን ትዕዛዝ መከተል አልፈልግም (ማቴዎስ 15፡9)፡፡ ጌታ የሱስ ከኢስልምና ጨለማ ነጻ አውጥቶ ወደሚያስደንቅ ብርሃን ሊያመጣኝ ፈለገ፡፡ ይሄውም “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው፡፡ ሕይወታችንን በሚመለከቱ ጉዳዮችና እግዚአብሔርን ስለማምለክ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሕገመንግስት ወደምትቀበለው ወደዚህች ቤተክርስቲያን ከመምጣቴ በፊት ብዙ ደረጃዎችን አልፌአለሁ፡፡
በትክክለኛው ቦታ እንድጠመቅ ስለመራኝ ጌታን አመሰግነዋለሁ፡፡ ትዕግስትና ጥበብን ሰጥቶኝ የእርሱን ሙሉ ትዕዛዙንና የኢየሱስን እምነት የምትጠብቀውን ቤተክርስቲያን እንድመርጥ ስለመራኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ሌሎች አብያተክርስቲያናት ምን ያክል ከእውነት እንደራቁ ተረዳሁ፡፡ በእነርሱ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝን ብዙ ነገርም አየሁባቸው (ለምሳሌ የጣኦት አምልኮ፣ ሰንበት አለመጠበቅ፣ ወደቅዱሳን መጸለይ፣ በማርያም ስም መጸለይ፣ የሚደጋገሙ ጸሎቶች፣ የወንጌል ሥርጭትን መፍራት፣ የእምነት ግብዝነት እና ሌሎችም)፡፡
ብዙ የይስሙላ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ በሰው እጅ የተሰሩ የባዕድ አማልክትን ስላመኑ እምነተታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የራቀ ነው፡፡ ባለሁበት ቤተክርስቲያን ውስጥ መጠመቄ ከጌታ የተቀበልኩት ትልቁ ስጦታዬ ነው፡፡ ለእርሱ እንድታመን፣ በመንፈስ በመጸለይ ታማኝ እንድሆን፣ ቃል እንዳነብና እዳገለግል ጌታ የሱስ አስተማረኝ፡፡ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ” (ሮሜ 12፡11-12)፡፡
አሁን ሕይወቴን ከነዚህ የምዕመናን ህብረት ጋር እመራለሁ፡፡ ይሄውም የተጠመቅሁበት ቤተክርስቲያኔ ማለቴ ነው፡፡ በጸሎት፣ በትዕግስትና በአገልግሎት ከምስጋና ጋር በጌታዬ በየሱስ ጸጋ እተጋለሁ፡፡ አብረውኝ የሚያመልኩ ምዕመናን ለሌሎች እንዴት እንደሚጸልዩ፣ በንግግራቸው እግዚአብሔርን ከፍ እንደሚያደርጉና እንደሚያመሰግኑት፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛትና የኢየሱስን ምስክርነት እንደሚጠብቁ ተመልክቼአለሁ፡፡ በእምነታቸው የሞቁ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሕይወታችው ሕገመንግስት የሚቀበሉ፣ ኢየሱስን ታላቁ አርአያቸውና የቤተክርስቲያኒቱ ራስ አድርገው የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው ጌታን ይታዘዙታል፡፡ ያለምንም አድሎ ሰውን ሁሉ ያከብራሉ፡፡ ሌሎች እንደሚያደርጉም ሌሎች ኃይማኖቶችን አያጠቁም፡፡ ከሌሎች የክርስትና ተቋማት ሕብረት ጋር ሳጠና በቤተክርስቲያኔ ላይ ያለውን ጥቃት አየሁ፡፡ ይህን ስል ባለማወቅ ወይም አንደኛውን ቡድን ለመደገፍ ብዬ አይደለም፡፡ ጌታ የሱስ ባስተማረኝ መሠረት በቅንነትና በታማኝ ልብ ሆኜ ነው ይህን የምናገረው፡፡
ለሚያስቸግረኝ ማንኛውም ጉዳይ ሁል ጊዜ ከጌታ እውቀትንና ጥበብን እለምናለሁ፡፡ ለጌታ ታማኝ አገልጋይ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ጌታ የሱስ ከሦስት አመት በፊት በሕልም ከተገለጠልኝ ወዲህ በክርስቶስ ማመን ጀመርኩ፡፡ በችኮላ አልተጠመቅሁም፤ ስለዚህ ክርስቶስ ጌታዋ በሆናት ቤተክርስቲያን እንድጠመቅ ስለፈለገ ጌታ ትዕግስቱን እንደሰጠኝ አሁን አስተውላለሁ፡፡
ሁላችንም በዚህ ምድር ላይ እንግዶች ነን፤ ምክንያቱም ስንሞት ማወደስና ማገልገል አንችልም፡፡ ምክንያቱም የተስፋ ቃሉን ሊፈጽምላቸው ክርስቶስ ቅዱሳንን ለመውሰድ መምጣቱን በእንቅልፍ ውስጥ ሆነን እንጠባበቃለን፡፡ “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐንስ 14፡1-3)፡፡
ጌታ ወደ ትክክለኛው ጥምቀት እንዲመራኝ ለረጅም ጊዜ ጠበቅሁት፡፡ ጌታ ትክክለኛውን ጊዜ፣ ቦታና ሰው እስኪያዘጋጅልኝ ድረስ ምእመናን ይጸልዩልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን መጠበቅ ከባድ ነበር፡፡ በየምሽቱ እንዲህ ብዬ እያለቀስኩ እጸልይ ነበር፡- “ጌታ ሆይ እርዳኝ፤ ትዕግስት፣ ጥበብና ጥንካሬም ስጠኝ፡፡ ምክንያቱም የምጠመቅበት ጊዜን መጠበቅም ሰልችቶኛል፡፡”
በመጨረሻም የጥምቀቴ ቀን ደረሰ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ደስታና ጉጉት ስለተሰማኝ ምሽቱን እንቅልፍ አልወሰደኝም፡፡ ቤተሰቦቼ እቅዴን ሰምተው ፍላጎቴን ሳላሳካ እንዳያደናቅፉኝም ስጋት ነበረኝ፡፡ ልክ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሄድ ሰው በጣም በማለዳ ተነስቼ ተሰናዳሁ፡፡ ምን ላደርግ እንደነበረ ለቤተሰቦቼ አልገለጽሁም ነበር፡፡ ለእራቴ ከእነሱ ጋር ተቀምጨ እያለሁ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኝ ነበር፤ ነገር ግን ሐዘንም ነበረኝ፡፡ ሳልነግራችሁ እየሄድኩ ስለሆነ ይቅር በሉኝ ብዬ በልቤ አሰብኩኝ፡፡ ፋጡማ ሆኜ ነው የምሄደው፤ ነገር ግን ሩት ሆኜ ነው የምመለሰው፡፡ ጌታ ኢየሱስ እጠብቅሻለሁ ስላለኝ ምንም ክፉ ነገር አይደርስብኝም፡፡ እወዳችኃለሁ፣ ነገር ግን ጌታን ደግሞ ከእናንተ በላይ እወደዋለሁ፡፡ ልክ ሌላ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደምሄድ ቦርሳዬን ከጀርባዬ ላይ አድርጌ ወጣሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጋ ስደርስ ወደሚያጠምቀኝ ፓስተር የሚወስደኝን ታክሲ ጠራሁ፡፡ ታክሲውን እየጠበቅሁ ሳለሁ አንድ ጓደኛዬ ከእኔ ጋር እንድትሄድ ጋበዝኩኳት፡፡ ዘገኘች፤ የቀረችም መሰለኝ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይመስገን፤ ክፍለ ዘመን የሚመስል አንድ ሰዓት ዘግይታ ብቅ አለች፡፡
ወዴት እንደምሄድ ማንም እንዳያውቅ በማለት ከጥምቀቴ ቦታ በጣም ወደሚርቀው ወደ ፓስተሩ ቤተሰብ ቤት ሄድን፡፡ በመጨረሻም ወደ ቤታቸው ደረስን፡፡ ከዚያም ብዙ የቤተክረስቲያን ወንድሞችና እህቶች ወደሚጠብቁን ወደ ጥምቀት ቦታው አመራን፡፡ አዲሱ ቤተሰቤ በጥምቀቴ ቀን ደስታዬን ሲካፈሉ ማየት ምንኛ ደስ ያሰኛል! አብረን ጸለይን፣ አለቀስንም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል አነበብን፣ ስሙንም አወደስን፡፡ ከዚያም ታሪኬንና ጉዞዬን እምባችንን እየዘራን ነገርኳቸው፡፡
ጊዜው ደረሰና ወደ ወንዙ ውስጥ ገባሁ፡፡ ፓስተሩ ሲጸልይ እንዲህ አልኩኝ፡- “ጌታ ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን፡፡ የሱስ እወድሃለሁ!” ልቤ አፌን ቀደመው፤ ጮክ ብዬ ቃላቶቹን ማዉጣት አማረኝ፡፡ ከዚያም ተጠመቅሁኝ፡፡ የጌታ አገልጋይ ከውሃ ስር ሲያጠልመኝ አሮጌው እኔነቴ ተገፎ በእርግጥ አዲስ ፍጥረት ሆንኩኝ፡፡ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” (2ቆሮ 5፡17)። ፋጡማ ሆኜ ረጂም መንገድ ከተጓዝኩ በኋላ ሩት ሆንኩኝ፡፡ አይኖቼ እንባ አቀረሩ፤ ድምፄን ሰምቶ ስለመለሰልኝ ጌታን አከበርኩት፡፡ ቦታው የተቀደሰ ነበር፡፡ በእምነት፣ ጥልቅ በሆነ ጌታን በማክበር ስሜት የተሞላ ነበር፡፡ በእርግጥም በጌታ ወንድሞቼ በሆኑ ሰዎች፣ መላእክቱና መንፈስ ቅዱስ ባሉበት የተደገሰ ሰርግ ነበር፡፡
ጥምቀቱ ወደ ሁለት ሰዓት ተኩል ፈጀ፡፡ ከዚያም ወደ ቤት ተመለስኩኝ፡፡ ከቀኑ በ7 ሠዓት ነበር ቤቴ የደረስኩት፡፡ ወንድ አያቴና ቤተሰቦቼ በማዕድ ተቀምጠው ነበር፡፡ ምግቡን አቀረብኩላቸሁ፡፡ ከአጠገባቸው ቁጭ ብዬ ቀኑ በጣም ያማረ እንደነበረ ነገርኳቸው፡፡ ከዚያም ወደ መኝታ ክፈሌ ገብቼ አለቀስኩኝ፡፡ ለእነርሱ ካለኝ ፍቅር የተነሳ እነርሱም ጌታ ኢየሱስን እንዲያውቁትና እንዲጠመቁ ተመኘሁ፡፡ ነገር ግን በልቤ እንዲህ አልኩኝ፡፡ አምላካችን መሃሪ ነው፤ በክርስቶስ ጠንካራና ጽኑ እሆናለሁ፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ቆይቼ እጸልይላቸሃለሁ፡፡ የክርስቶስ አምባሳደር እሆናሁ፡፡ እንግዲህ “እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን” (2ቆሮንቶስ 5፡20)።
ሁኔታዬ ቀላል ስላይደለ እንድትጸልዩልኝ እፈልጋለሁ፡፡ እምነቴን ከቤተሰቦቼ በመደበቅ በጌታ የሱስ ጥበቃ ስር መኖር አለብኝ፡፡ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” (2ጢሞቴዎስ 3፡12)።
ጌታ ኢየሱስን አውቀው የቅሬታዋ ቤተክርስቲያን አካል ይሆኑ ዘንድ እባክዎን ለቤተሰቦቼና ለሌሎችም ሙስሊሞችም ጸልዩልኝ፡፡ በጠባቡ በር የሚገባው ሁሉም ሰው ሳይሆን ሕይወቱን ለጌታ የሚሰጥና አማኞችን የሚገጥማቸውን ጨለማ የሚቋቋም፣ የጌታን ዱካ የሚከተል እና ትዕዛዙንና እምነቱን የሚጠብቅ ሰው ብቻ ነው፡፡