የያቁብ (የያዕቆብ) ሕልሞች

ያቁብ ወንድሙን ከበደለው በኋላ ከእርሱ ሸሸ፡፡ ሲሸሽም ብቸኝነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰማው፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ መነቃቃት እንዲኖረው፣ ከአላህ ጋር እውነተኛ ግንኙነት እንዲኖረው፣ ለአላህ ቃሎች የታመነ እንዲሆን፣ የአላህ በረከትና ጥበቃ ከእርሱ ጋር እንደሚሆን ሊያሳየው አላህ ሕልም ሰጠው፡፡

“ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ። በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ። እግዚአብሔርም ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ (. . .) እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። (ታውራት ዘፍጥረት 28፡10-16)።

ከዚያ በኋላ ያቁብ በዚያ ሥፍራ አላህን አመለከ፤ ከእርሱም ጋር የቀረበ የግል ሕብረት ማድረግ ጀመረ፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ ያቁብ ወደ ላባን ምድር እንዲሄድ አላህ መራው፤ ለላባንም ብዙ አመት ሠራለት፤ ሴት ልጆቹንም አገባ፡፡ የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት፤ የአላህም በረካ በእርሱ ላይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት አማቱ ሊያታልለው ፈለገ፡፡ “ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ አልተለየኝም፤ መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም። አባታችሁ ደሞዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጐዳኝ እግዚአብሔር አልፈቀደለትም” (ተውራት ዘፍጥረት 31፡4-7)። ከዚያም አላህ ለያቁብ ሌላ ሕልም ሰጠው፡- “እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት። እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤ የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅና ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ” (ታውራት ዘፍጥረት 31፡10-13)፡፡ በዚህ ሕልም አላህ ሕይወቱን እንደሚመራውና የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሰጠው ለያቁብ አሳየው፡፡

እንደገና፣ አላህ ሰዎችን ለመምራትና ፈቃዱን ሊገልጥላቸው፤ ለሚፈልጉትም እውነቱን ሊገልጥ በሕልም መጠቀም እንደሚችል እናያለን፡፡

More Stories
There Is Only One God
አማርኛ