በክታበል ሙቀደስ (መጽሐፍ ቅዱስ) እና በቁራን ውስጥ ከምናገኛቸው ተመሳሳይ ታሪኮች ይሄኛው ከሁሉም ይልቅ ተመሳሳይ ነው፡፡ ታውራት ዘፍጥረት 37ኛው ምዕራፍ ስለ ዩሱፍ ታሪክ ያወሳል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ይህ ሕልም በቁራን 12ኛው ሱራ ውስጥ ይገኛል፡፡ ዩሱፍ ከአላህ ሕልምን የተቀበለበት ታሪክ ነው፡፡
“ዩሱፍ ለአባቱ፤- አባቴ ሆይ! እኔ ዐስራ አንድ ከዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃንም (በሕልሜ) አየሁ፡፡ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው” - ሱረቱ ዩሱፍ 12፡4፡፡
“እንደ ገናም ሌላ ሕልም ዐለመ፤ ለወንድሞቹም፣ ‘እነሆ፤ ሌላ ሕልም ዐለምሁ፤ ፀሓይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ’ ብሎ ነገራቸው።ሕልሙን ለአባቱና ለወንድሞቹ በነገራቸው ጊዜ፣ አባቱ ‘ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?’ ሲል ገሠጸው። ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው” (ታውራት ዘፍጥረት 37፡9-11)::
የዩሱፍ ወንድሞች ቀኑበት፤ የዩሱፍ ሕልም ደግሞ ንዴታቸውን የበለጠ አጠነከረ፡፡ ስለዚህ ዶልተውበት ለባርነት ወደ ግብጽ ምድር ሸጡት፡፡ አላህ ሁሉን ነገር አውቋል፤ ለዩሱፍና ለቤተሰቦችም ዕቅድ ነበረው፤ የተቀበለውም ሕልም ወደፊት ሊሆን ያለውን የሚያሳይ ራእይ ነበር፡፡ በግብጽ ምድር ዩሱፍ በታላቅና ተሰሚነት ባለው ሰው ቤት አገለገለ፡፡ ሚስቱ ዩሱፍ ሊደፍረኝ ነበር ብላ ስለከሰሰችው ይህ ሰው ዩሱፍን ወይኒ ቤት አወረደው፡፡ ነገር ግን አላህ ለሁሉም ነገር ዕቅድ ነበረው (ታውራት ዘፍጥረት 39)፡፡
“በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ባሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር። የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው። የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው እንጂ” (ታውራት ዘፍጥረት 40፡20-23)።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግብጽ ንጉስ ፈርዖን ሕልም አለመ፤ ሕልሞቹንም የሚተረጉምለት ጠፋ፡፡ በመጨረሻም ጠጅ አሰላፊው ፈጣሪና እውነተኛ አምላክን የሚያመልከውን ዮሴፍን አስታወሰው፡፡ ዮሴፍም ወደ ንጉሱ እንዲቀርብ ተጠራ፡፡ ከጸለየና ጥበብ እንዲሰጠው አላህን ከለመነ በኋላ ለንጉሡ የሕልሙን ትርጉም ነገረው፡- “ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ ‘ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። አስቀድሜ ለፈርዖን እንደ ተናገርሁት፣ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል” (ታውራት ዘፍጥረት 41፡25-28)።
ከዚህ በኋላ ዩሱፍ ንጉሡ በሰባቱ የረሃብ አመታት እህል በትክክል ተቆጣጥሮ የማዳረስ ችሎታ ያለውን ሰው እንዲመድብ መከረው፡፡ “ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። “እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም” (ታውራት ዘፍጥረት 41፡32-33)። ንጉሡም ለሰባቱ የረሃብ አመታት የእህል አቅርቦቱን እንዲቆጣጠር ዩሱፍን ሾመው፡፡ መጀመሪያ ላይ እርሱ አላወቀም፤ ነገር ግን እርሱ ያከፋፈለው እህል በግብጽ ምድር የነበሩትን የብዙ ሺህዎችን ሕይወትና የቤተሰቡን - የአባቱንና ለባርነት የሸጡትን የወንድሞቹን - ሕይወት ታደገ፡፡ በኋላ ከወንድሞቹም ጋር ተነጋገረ፤ ታረቁም፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ ሕልም በተጨባጭ በሰዎች ሕይወት እንደሚፈጸም ከሦስቱ ሕልሞች - ከዮሱፍ ሕልም፣ ከሁለቱ እስረኞች ሕልምና ከንጉሡ ሕልም - በግልጽ እናያለን፡፡ ያመኑትም ተባርከዋል፡፡