ነቢዩ ዳንኤል ከአላህ ነቢያት መካከል አንዱ ነው፡፡ በቁርዓን ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ነገር ግን በሐዲዞችና በእስልምና ትውፊቶች ውስጥ ስለእሱ ማንበብ እንችላለን፡፡ ሙሉ ታሪኩን በታውራት ውስጥ እናገኛለን፡፡
ናቡከድናፆር ሌላ ሕልም አልሞ ነበር፤ ይሄኛውንም ዳንኤል ነበር የተረጎመለት፡፡ ንጉሱ ዙፋኑን ገና እያደላደለ በነበረበት ዘመን ያየው የመጀመሪያ ሕልሙን ካየ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ሁለተኛው ሕልሙን ያየው ታላላቅ ፕሮጀክቶቹ ካለቁ በኋላ ነበር፡፡ ስልጣኑም ገኖ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ባቢሎን በዓለም ላይ ታላቋ ሃያል መንግስት ነበረች፡፡ ነገር ግን ከአላህ ኃይልና ስልጣን ጋር የሚስተካከል ሌላ ኃይል ፍጹም የለም፡፡
“በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረዥም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ። ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር። ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከእርሱ ይመገብ ነበር” (ዳንኤል 4፡10-12)፡፡ ታላቁና የሚያምረው ዛፍ እንደሚቆረጥና ፍሬዎቹም እንደሚበተኑ፣ ከሥሩም የተጠለሉ ወፎችና የዱር አራዊት እንደሚበተኑ፣ ጉቶውና ሥሩ ግን በምድር አፈር ውስጥ በብረትና በናስ እንደሚታሰር ከሰማይ ያለ አካል ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ “በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየሁት ራእይ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘ዛፉን ቍረጡ፤ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ ከሥሩ ያሉት እንስሶች፣ በቅርንጫፎቹም ላይ ያሉት ወፎች ይሽሹ። ነገር ግን ጕቶውና ሥሩ በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ። “ ‘በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ በጥሻም ውስጥ ከአራዊት ጋር ይኑር” (ዳንኤል 4፡13-15)።
የአላህ በረከት በዳንኤል ላይ እንዳለ ንጉሡ ስለተገነዘበ፤ ሕልሙን እንዲተረጉምለት ጠየቀው፡፡ ነቢዩም አሁን የተሻለ ልምድ አካብቶ ነበር፤ የሕልሙንም ራዕይ ሲሰማ ደነገጠ፤ ለንጉሡም ሁሉንም ነገር ነገረው፡፡ “እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣ ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጐጆ መሥሪያ ያለው፣ ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ። ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቍረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጕቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንደ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ። “ንጉሥ ሆይ፤ ትርጕሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤ ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል። የዛፉ ጕቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለስልህ ያመለክታል። ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል” (ዳንኤል 4፡20-27)፡፡
ከትዕቢቱ የተነሳ ናቡከድናፆር ከሰዎች መካከል ተሰድዶ ከሜዳ አራዊት ጋር እንዲኖር ተደረገ፡፡ ሰባቱ አመታት እስኪያልፉ ድረስ ከበሬ ጋር ሣር በላ፤ አላህ በሰዎች መንግስታት ላይ ስልጣን እንዳለውና ለፈለገውም እንደሚሰጥ ተገነዘበ፡፡ በዚህ ጊዜ መንግስቱ ተጠብቆ ይቆየዋል፤ ልቡንም ከቀየረ ወደ መንግስቱ ይመለሳል፡፡ በትሕትና ሐጢያቱን ቢናዘዝ ምናልባት አላህ ይምረውና ብልጽግናውን ያሰፋለት ይሆናል ብሎ ነቢዩ ዳንኤል ንጉሱን መከረው (ቁ. 27)፡፡
ከአሥራ ሁለት ወራት በኋላ ንጉሱ በቤተመንግስቱ ውስጥ ሲመላለስ ስለገነባት ስለ ታላቋ ባቢሎን በትዕቢት ሲናገር አላህ በሕልሙ ቀድሞ ነግሮት የነበረውን ፍርድ ተገበረ፡፡ ወዲያውኑ ናቡከድናፆር እንደ ዱር አራዊት መሆን ጀመረ፡፡ ልክ ዳንኤል እንዳለው ከሰባት ዓመታት በኋላ ማስተዋሉ ተመልሶለት ወደ ባቢሎን መንግስት ተመለሰ፡፡ አላህም በአለማት ሁሉ ላይ ሐያልና የበላይ ባለሥልጣን መሆኑን ተገነዘበ (ቁ. 36-37)፡፡
- 1. አላህን እንጂ ጣዖታትን ማምለክ እንደሌለብን
- 2. አላህ ሁሉንም የሚቆጣጠር መሆኑንና ለፈቃዱ መገዛት አስፈላጊ መሆኑን
- 4. አላህ በሕልም እንደሚናገረን፡፡