“ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ ዐዋቂ፣ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው” (ማቴዎስ 22፡35-40)፡፡
ኢሳ አል-መሲህ ስለ ይቅርታ ያስተማረው ትምህርት ከመልዕክቱ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ይበድሉናል፤ የበደለንን ሰው ይቅር ማለት ይከብደናል፡፡ ይህም የሆነው ማሕበረተሰቡ ይህን እንደ መስፈርት አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ለስሕተታችና ለሐጢያታችን አላህ ይቅር እንዲለን ስንጠይቀው እኛም ተመሳሳይ ይቅርታ ለበደሉን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን መገምገም አለብን፡፡ ኢሳ ስንት ጊዜ ይቅር መባባል እንዳለብን ሲጠየቅ እንዲህ ብሎ ነበር የመለሰው፡- “እስከ ሰባት ጊዜ አልላችሁም፣ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ”
ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሊያስረዳን የሚከተለውን ምሳሌ ሰጠ፡-
“ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በአገልጋዮቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። ሂሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺሕ ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት። አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። በዚህ ጊዜ አገልጋዩ እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። ጌታውም ዐዘነለትና ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው። “ያ አገልጋይ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር የእርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ ዕንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው። “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው። “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው። የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም ዐዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት። “በዚህ ጊዜ ጌታው አገልጋዩን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው። “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል” (ማቴዎስ 18፡23-35)፡፡ (Matthew 18:23-35 ESV)
ከጓደኛ ወይም ከጎረቤት ጋር ያለንን ግጭት እንዴት መፍታት እንዳለብን ኢሳ እና ኢንጂል ምን ያስተምሩናል?
“ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፣ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ”.…(ማቴዎስ 5፡23-24)።.
አንዳንድ ጊዜ አላህን እናገለግላለን እያልን ነገር ግን ከአላህ ልጆች አንዱን እንበድላለን፡፡ ኢሳ ያስተማረው፣ አላህን ለማምለክ ስንቀርብ፣ ሌሎችን በድለን ከሆነ በመካከላችን ያለውን ጉዳይ ለማስተካከል የተቻለንን ሁሉ ስለማድረጋችን ህሊናችን ንጹህ መሆን አለበት፡፡ ይህ ማለት ግን ሁል ጊዜ ሰዎች ይቀበሉናል ማለት አይደለም፡፡ ሊጠሉን ይችላሉ፤ ነገር ግን እኛ ጉዳዩን ለማስተካከል የቻልነውን ያህል ጥረናል፡፡
የአላህ ሰዎች የአላህን ፍቅር ማንጸባረቅ አለባቸው፤ ለዚህም ነው ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የምንጥረው፡፡ “ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወድደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና” (1ዮሀንስ 4፡20) ።
ሰውን መጥላት ከባድ ችግር ነው፡፡ ሰዎችን ሳንጠላ ክፉ አካሄዳቸውንና ድርጊታቸውን ልንጠላ እንችላለን፡፡ “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ” (1ዮሀንስ 3፡15)።
ኢሳ እና ኢንጂል በሚያስተምሩት መሰረት በማንም ሰው ላይ ቂም ወይም ጥላቻ ልንይዝ አይገባም፡፡ የአላህን እውነተኛ ፍቅር ልንገነዘብና ለሌሎችም ልናንጸባርቅ ይገባል፡፡
ለበለጠ ጥናት፡-
1. ሌሎች ሰዎች ቢጠሉን እኛ ልዩ ለመሆን ፈቃደኞች መሆን አለብን፡ ሉቃስ 14፡26
2. የአላህ ፍቅር፡ - 1ዮሐንስ 4፡8
3. አላህን በመከተላችን ሰዎች ሲበድሉንና ሲጠሉን፡ ማቴዎስ 5፡10፡፡